ቀጥታ፡

በጌዴኦ ዞን ከተሞች ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ ለመከላከል ለአርሶ አደሮች ጊዜያዊ መጠቀሚያ ሰነድ ይሰጣል

ዲላ ህዳር 3/2011 በጌዴኦ ዞን በከተሞች ማስፋፊያ አካባቢ የሚስተዋለውን ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ ለመከላከል ለአርሶ አደሮች ጊዜያዊ መጠቀሚያ ሰነድ እንደሚሰጥ የዞኑ ከተማ ልማትና ቤቶች መምሪያ ገለጸ፡፡ መምሪያው የ2010 ዕቅድ አፈጻዕምና የ2011 ዕቅድን አስመልክቶ ዞናዊ የሴክተር ጉባዔ አካሂዷል ፡፡ የመምሪያው ኃላፊ ወይዘሪት የምሥራች ገመዴ በዚሁ ወቅት በዞኑ በተለይ ከተሞችን ከዙሪያ ወረዳዎች በሚያገናኙ የማስፋፊያ አካባቢዎች ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ ሁለንተናዊ ዕድገታቸውን በሚያቀጭጭ  መልኩ እየተስፋፋ ነው። በዚህም በአካባቢዎቹ የሚካሄደው ሕገ-ወጥ ተግባር ከተሞች ከፕላን ውጭ እንዲስፋፉ ማድረጉን አመልክተዋል። ሕገ-ወጥ ግለሰቦች በሚፈጽሙት ወረራና ግንባታ አርሶ አደሩ መሬቱን በመሸጥ ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ እየተፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል ፡፡ ድርጊቱን ለመከላከል በየደረጃው ባለው ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍና ግብረ-ኃይል ቢቋቋም፤ውጤት አለማስገኘቱን የተናገሩት ወይዘሪት የምሥራች፣ባለፈው ዓመት ወደ መሬት ባንክ የተመለሰው 30 ሄክታር መሬት መመለሱን በአብነት አቅርበዋል። መመሪያው አርሶ አደሮቹ ይዞታቸውን ለግብርና አገልግሎት እንዲጠቀሙበት የሚፈቅድ መሆኑን ያስረዱት ኃላፊዋ፣ይዞታው ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ላፈሩት ንብረት በሕግ አግባብ ካሳ ተከፍሏቸው ለራሳቸውና ከ18 ዓመት በላይ ለሆኑ ልጆቻቸው በከተማ ውስጥ የቤት መሥሪያ ቦታ ይቀርብላቸዋል ብለዋል፡፡ የይርጋጨፌ ከተማ ከንቲባ አቶ መልካሙ ሺፈራው በበኩላቸው በከተማው ውስጥ ከመሬት ካርታ ውጭ ትርፍ ይዞታ መያዝ፣መከለልና ሕገ-ወጥ ግንባታ እንደሚካሄድ አመልክተዋል፡፡ ወረራውን ለመከላከል አስተዳደሩ በማስፋፊያ አካባቢ ከሚገኙ አርሶ አደሮች ጋር እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ አስተዳደሩ ባለፈው ሩብ ዓመት በከተማው 3ሺ159 ካሬ ሜትር በግለሰቦች በትርፍ ይዞታ የተያዘ መሬት በኦዲት አግኝቶ ለመሬት ፈላጊዎች በሊዝ ዋጋ ማቅረቡን ተናግረዋል ፡፡ ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ በከተማ መሠረተ ልማት ዝርጋታን ከማስተጓጎል ባለፈ ፕላንን መሠረት ያደረገ እድገት እንዳይኖር ተፅዕኖ እንደሚያሳድር የገለጹት የዲላ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት አልማስን ናቸው፡፡ አምና በከተማዋ በወረራ ተይዞ የነበረ 3 ነጥብ 3 ሄክታር ወደ መሬት ባንክ መግባቱን አስታውቀዋል፡፡ ወረራውን ከመከላከል ባሻገር የከተማዋን የመሬት ጥያቄ ጫና ለመቀነስ ለመኖሪያና ለኢንቨስትመንት ቦታ በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ በተያዘው ሩብ ዓመት ስድስት ሄክታር መሬት ለማቅረብ ዝግጅቱን መጠናቀቁን አቶ ጌትነት አስረድተዋል፡፡ በጉባዔው የዞን፣የከተሞችና የወረዳ አስተዳደር ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል ፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም