በአማራና ደቡብ ክልሎች የመኸር ሰብል በዘመቻ እየተሰበሰበ ነው

71
አዳማ ህዳር 3/2011 በአማራና በደቡብ ክልሎች በመኸር ወቅት የለማውን ሰብል ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ለመከላከል ምርትን በዘመቻ  እየተሰበሰበ ነው፡፡ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የዕቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ድልነሳው እንዳስታወቁት ምርቱ እየተሰበሰበ ያለው በክልሉ በ2010/11 የመኸር ወቅት በተለያዩ ሰብሎች ከለማው ነው። የደረሰ ሰብልን ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ለመከላከል በተሰራው ሥራ በመኽሩ ከለማው 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር ማሳ ውስጥ እስካሁን ከ707 ሺህ ሄክታር በላይ በሆነ መሬት ላይ የለማው ሰብል ተሰብስቧል። አጠቃላይ ከለማው መሬት ውስጥ ከ652 ሺህ 774 ሄክታር በሚሆነው መሬት ላይ የለማው የኤክስፖርት ሰብል መሆኑንም አቶ መንግስቱ ገልጸዋል። አቶ መንግስቱ እንዳሉት በምርት ማሰባሰብ ሥራው ላይ አባውራና እማውራ አርሶ አደሮች በልማት ቡድን ተደራጅተው በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ። ከምርት ዘመኑ ከክልሉ 110 ሚሊዮን 300 ሺህ ኩንታል ምርት የሚጠበቅ ሲሆን ይህም ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ እንዳለው ተመልክቷል። እንደ አቶ መንግስቱ ገለጻ በመኽር ልማቱ በክልሉ በተለያዩ ወረዳዎች 100 ሺህ ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ ተከስቶ የነበረውን ተምች በኬሚካልና በባህላዊ መንገድ ለመከላከል በተደረገው ጥረት 83 በመቶ የሚሆነውን  ሰብል መከላከል ተችሏል። በተመሳሳይ መልኩ በደቡብ ክልል በመኽሩ ከ874 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የለማውን ሰብል የማሰባሰብ ሥራ መጀመሩን  የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ አስታውቋል። የቢሮው ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ እንዳሉት ለምርት ስብሰባው አጭደው የሚወቁ 81 ኮምባይነሮችን በመጠቀም በ11 ሺህ 727 ሄክታር መሬት ላይ የነበረው ምርት መሰብሰብ ተችሏል። ምርትን ከብክነት ለመታደግ የስንዴ ማጨጃ፣ በሞተር የሚሰራ የበቆሎ መፈልፈያና አነስተኛ የመውቂያ ማሽኖች ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑንም ነው የገለጹት። በምርት ማሰባሰቡ ሥራ 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን አርሶ አደሮች የሚሳተፉ ሲሆን 46 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎም ይጠበቃል። በምርት ዘመኑ ከ6 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የተከሰተው ተምች ካጋጠሙ ተግዳራቶች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቁመው "ተምቹን በእጅ በመልቀምና ኬሚካል በመርጭት መከላከል ተችሏል" ብለዋል። የቢጫ ዋግ በሽታም በ18 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ ተከስቶ ፀረ - ፈንገስ ኬሚካል ርጭት በማካሄድ መቆጣጠር መቻሉን ነው አቶ ጥላሁን ያስረዱት።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም