በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተፈጠረው ሰላም ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋጽኦ አለው

አዲስ አበባ ህዳር 2/2011 በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተፈጠረውን ሰላም መሰረት በማድረግ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማረጋገጥ እንደሚቻል የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ገለጹ። የሁለቱን አገሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር በአፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ወርቅሰም ማሞ የተመራ የልዑካን ቡድን ወደ ኤርትራ ተጉዞ ነበር። በአፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ወርቅሰም ማሞ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈጠረውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስመዝገብ ይቻላል። የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ሰላም ከሆነ በአካባቢው ያሉ አገሮች በትራንስፖርት፣ በኤሌትሪክ ኃይልና በሌሎች የመሰረተ ልማት አውታሮች ትስስር ለመፍጠር እንደሚያስችላቸውም ተናግረዋል። አፈ-ጉባዔዋ እንዳሉት፤ የአማራ ክልል ህዝብ በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈጠረውን ሰላም በመደገፍ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ምክክር ለማድረግ አንድ የልዑካን ቡድን ወደ ኤርትራ እንዲጓዝ ተደርጓል። የልዑካን ቡድኑ በኤርትራ በተደረገለት መልካም አቀባበል እንደተደረገላቸው ያስታወሱት አፈ-ጉባዔ ወርቅሰም የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለሦስተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ጉብኝት እንዲያደርጉ ያደረገላቸውን ግብዣ ተቀብለው በመምጣታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን የሚያጠናክርና በአገሮቹ መካከል በመተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማምጣት ያስችላል ብለዋል አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ወርቅሰም። በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው ኢትዮጵያና ኤርትራ የታሪክ ትስስር ያላቸው አገሮች በመሆናቸው ከህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ባሻገር ከሶማሊያ ጋር በመተባበር የሚያከናውኗቸው ተግባራት በቀጠናው ሰላም መስፈን ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል። ኤርትራና ሶማሊያ የባህር በር ያላቸው አገሮች በመሆናቸው ኢትዮጵያ ከአገሮቹ ጋር የምታደርገው ግንኙነት ኢኮኖሚያዊ ትስስርን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ሰሜንና ሰሜን ምዕራብ ክፍል የሆነው የአማራ ክልል ከኤርትራ ህዝብ ጋር የታሪክ ቁርኝት ያለው በመሆኑ የሁለቱን አገሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚረዳም አቶ ንጉሱ ተናግረዋል። በአማራ ክልል ለሁለት ቀናት ጉብኝት ያደረጉት የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂና የሶማሊያ ፕሬዝዳንት መሐመድ አብዱላሂ በማዕከላዊ ጐንደር ዞን በምዕራብና ምስራቅ ደንቢያ ወረዳዎች የሚገኘውን የመገጭ ስራባ የመስኖ ኘሮጀክትን ጎብኝተዋል። እንዲሁም የቡሬ አግሮ ኘሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጐብኝተዋል። የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያስገነባውን የጥበበ ጊዮን ሪፈራል ሆስፒታልን መርቀው መክፈታቸውም ይታወቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም