ተፈናቃይ አርሶ አደሮች የደረሰ ሰብላቸውን መንግሥት በመሰብሰብ እንዲያግዛቸው ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
ተፈናቃይ አርሶ አደሮች የደረሰ ሰብላቸውን መንግሥት በመሰብሰብ እንዲያግዛቸው ጠየቁ
ጊምቢ ህዳር 2/2011 በቤኒሻንጉል ጉሙዝና ምዕራብ ወለጋ ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች መንግሥት የደረሰ ሰብላቸውን ለመሰብሰብ እንዲያደግዛቸው ጠየቁ። በምዕራብ ወለጋ ዞን ሰባት ወረዳዎች አርሶ አደሮች በማሳ ላይ የሚገኘው ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብና በዱር አራዊት እየወደመባቸው መሆኑን ይናገራሉ። ከአርሶ አደሮቹ አንዳንዶቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት በአካባቢዎቹ በተከሰተው ግጭት በመፈናቀላቸው የደረሰ ሰብላቸውን ለመሰበስብ የመንግሥትን ድጋፍ ይሻሉ። ከነጆ ወረዳ የንበል ጋራኦሊ ቀበሌ ተፈናቅለው ከአምስት ቤተሰባቸው በነጆ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙት አርሶ አደር ረታ ታፈሰ በግማሽ ሄክታር ላይ የሚገኘው ሰብል በመሰብሰብ መንግሥት እንዲታደጋቸው ጠይቀዋል። ሌላኛው ከዚሁ ቀበሌ የተፈናቀሉት አርሶ አደር ባይሳ ገረሙ በበኩላቸው በመኸር ያለሙት ከግማሽ ሄክታር በላይ ሰብል በዱር እንስሳትና ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እየወደመባቸው መሆኑን ገልጸዋል። ከላሎ አሳቢ ወረዳ አሌ በሬዳ ቀበሌ ተፈናቅለው በዶንጎሮ መጠለያ ያሉት አርሶ አደር ተመስጌን ኡመታ በባህላዊ መስኖ ያለሙት በቆሎ፣ድንች ፣ ቃሪያና ቅመማ ቅመም ምርት ሳይሰበስቡ መፈናቀላቸውን ይናገራሉ። መንግሥት ምርታቸው የሚሰበሰብበትን ሁኔታ በማመቻቸት ከብክነትና ከኪሳራ ሊታደግልኝ ይገባል ብለዋል። የምዕራብ ወለጋ ዞን የግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሁንዴሳ ሊኪሳ በበኩላቸው በዞኑ ከ50 ሺህ የሚበልጡት አርሶ አደሮች መፈናቀላቸውንና ጉዳት እየደረሰበት ያለው ሰብል ከጥፋት ለማዳን ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አስታውቀዋል። የአርሶ አደሩ መተዳደሪያ የሆነው ሰብል ሳዳይባክን ለመሰብሰብ ለማከማቸት ከዞኑ የጸጥታና አስተዳደር ጽህፈት ቤት እንዲሁም ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ከተቋቋመው ግብረ ኃይል ጋር እየተሰራ መሆኑም ገልጸዋል። አርሶ አደሮቹ የጸጥታ ኃይሉ ጥበቃ እያደረገላቸው ምርታቸውን የሚሰበስቡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት እየተደረገ ነው። የሁለቱ ክልሎች አመራሮች ሰላም ለመመለስ ጥረት እያደረጉ በመሆናቸው ችግሩ እልባት ያገኛል የሚል እምነት እንዳላቸውም አቶ ሁንዴሳ አስረድተዋል።