አቶ ዳጋቶ ኩምቤ የወላይታ ዞን ተጠባባቂ ዋና አስተዳዳሪ ሆነው ተሾመ

ሶዶ ህዳር 1/2011 የወላይታ ዞን ምክር ቤት ስድሰተኛ የስራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ አቶ ዳጋቶ ኩምቤን የዞኑ ተጠባባቂ ዋና  አስተዳዳሪ አድርጎ ሾመ፡፡ ድርጅታቸውን በመወከል ተሿሚውን ለምክር ቤቱ ጉባኤ ያቀረቡት የወላይታ ዞን ደኢህዴን ንኡስ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤታ ኃላፊ አቶ ጥበቡ ዮሃንስ  የትምህርት ዝግጅትና ከዚህ በፊት በስራ ላይ የነበራቸው ቁርጠኝት ታይቶ ለቦታው  ብቁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በተጠባባቂ የተሸሙት አቶ ዳጋቶ ኩምቤ ከዚህ በፊት የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና ፍትህ መምሪያ  ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡ አዲሱ አስተዳዳሪ ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ  ህዝብን ለማገልገል የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ህዝቡም ከጎናቸው እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡ ሌሎች 10 አዳዲስ የመምሪያ ኃላፊዎች ለምክር ቤቱ ቀርበው ሹመታቸው መጽደቁም ተንግሯል፡፡ አዲስ የተሾሙትም ወጣቶችና ስፖርት፣ የእንስሳትና አሳ ሃብት፣ ጤና፣ ትምህርት፣ ጸጥታ አስተዳደር፣ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ፣ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት፣ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት፣ የፍትህ መምሪያ ኃላፊዎች ናቸው፡፡ አቶ ዳጋቶ ኩምቤ የተሾሙት የቀድሞው  አስተዳዳሪ ወደ ክልል የስራ ኃላፊነት በመሄዳቸውና ነባሮቹ የመምሪያ ኃላፊው በአዲስ የተተኩት ደግሞ የለውጡን ሂደት ለመደገፍ መሆኑን በጉባኤው  ተገልጿል፡፡ ምክር ቤቱ በ2011 ዓ.ም አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች በስራ እድል ፈጠራ፣ በህግ ማስከበርና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ወላይታ ክልል እንዲሆን የቀረበውን ጥያቄን ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ በማጽደቅ በዚህ ላይ ከህዝቡ ጋር ውይይት እንዲደረግና የደረሰበትን ለምክር ቤቱ እንዲያቀርብ ለአስፈጻሚ አካላት ኃላፊነት በመስጠት ለሁለት ቀናት ያካሄደው ጉባኤ ማምሻውን አጠናቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም