በትግራይ ክልል 12 ከተሞች በሚካሄደው ታላቁ ሩጫ ህብረተሰቡ እንዲሳተፍ ጥሪ ቀረበ

11
መቀሌ ግንቦት 15/2010 ''ስለ አባይ እረጣለሁ'' በሚል መሪ ቃል በትግራይ ክልል የፊታችን እሁድ በሚካሄደው ታላቁ ሩጫ  ህብረተሰቡ እንዲሳተፍ ጥሪ ቀረበ፡፡ በክልሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የህዝብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ጊዜያዊ አስተባባሪ አቶ ሀይለኪሮስ ጠዓመ ዛሬ እንደገለጹት ለታላቁ የኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ ለማሰባሰብ በአገር አቀፍ ደረጃ የተዘጋጀው ታላቁ ሩጫ በክልሉ መቀሌን ጨምሮ በ12 ከተሞች ይካሄዳል፡፡ ፡፡ በየከተሞቹ በሚካሄደው ሩጫ ከ48 ሺህ በላይ ህዝብ በመሳተፍ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ብር ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም ሩጫው የሚካሄድባቸው ከተማ ነዋሪዎች የመሮጫ ካኔተራ በመግዛት ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ያላቸውን አጋርነት እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል፡፡ ሩጫው ፀሃይ በሚበረታበት ሁመራ ከተማ  ከጥዋት 12 ሰዓት  እንደሚጀመርም አስታውቀዋል፡፡ በክልል ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ የህዝባዊ መሰረት ስፖርት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ካህሱ ዜናዊ በበኩላቸው  ለአገራዊ አንድነትና ፈጣን ልማት መረጋገጥ ትልቅ ሚና ለሚኖረው  የህዳሴ ግድብ ታላቁ ሩጫ  ሁሉም  እንዲሰተፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ''በታላቁ ሩጫ መሳተፍ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ አጋርነትን ከማረጋገጥ ባለፈ ለአካላዊ እንቅስቃሴ ጠቃሚ  ነው'' ብለዋል፡፡ ከትግራይ ክልል ለህዳሴ ግድብ ከህብረተሰብ ፣ ከመንግስት ሰራተኞች፣ ከንግዱ ማህበረሰብና ሌሎች ግለሰቦች  እስካሁን 500 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም