ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ነገ በሚካሄዱ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች ይሳተፋሉ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ነገ በሚካሄዱ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች ይሳተፋሉ
አዲስ አበባ ህዳር 1/2011 ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ነገ በሚካሄዱ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ። በስፔን በሚካሄደው ክሮስ ደ አታፑኤርካ አገር አቋራጭ ውድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የማሸነፉን የቅድሚያ ግምት አግኝተዋል። በሴቶች የስምንት ኪሎ ሜትር ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ የአገር አቋራጭ ውድድሩን ለሶስተኛ ተከታታይ ጊዜ ለማሸነፍ የምትሮጥ ሲሆን የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት እንደተሰጣት ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በድረ-ገጹ አስፍሯል። አትሌት ሰንበሪ ተፈሪ ከውድድሩ ሁለት ጊዜ አሸናፊ ሌላዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት በላይነሽ ኦልጅራ፣ ኬንያዊቷ ማርጋሬት ቼሊሞና በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ስዊድናዊ ከሆነችው ምዕራፍ ባህታ ከባድ ፈተና እንደሚጠብቃት ተገልጿል። በወንዶች ያለፈው ዓመት የውድድሩ አሸናፊ ኢትዮጵያዊው አትሌት ጌታነህ ሞላ የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት ተሰጥቶታል። የአምስት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ አትሌት ኢማና መርጊያ፣ አትሌት ሙክታር እድሪስና አትሌት አባዲ ሀዲስ በውድድሩ የሚሳተፉ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ናቸው። የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ውድድሩን አስመልክቶ ባወጣው የቅድመ ውድድር ዳሰሳ ዘገባ በወንዶቹ ውድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ማን ያቆማቸዋል? የሚል ጥያቄ ያነሳ ሲሆን ኬንያዊያን አትሌቶች በውድድሩ የኢትዮጵያ አትሌቶች ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ግምቱን አስቀምጧል። በስፔን የሚካሄደው ክሮስ ደ አታፑኤርካ አገር አቋራጭ ውድድር በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ፈቃድ ያለው ውድድር ነው። በቻይና ሄፌይ ዓለም አቀፍ ማራቶን በሴቶች ውድድሩን የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት ያገኘችው አትሌት አበራሽ ፈይሳ በወንዶች አትሌት ደረጀ ደበሌ ይወዳደራሉ። በሊባኖስ ቤይሩት ማራቶን በወንዶች አትሌት ሂርቦ ሸኖና አትሌት ገመቹ ኢዲኦ በሴቶች አትሌት አለምነሽ ሂርጳ፣ አትሌት መዲና ደሜና አትሌት ንግስት ሙሉነህ ይሳተፋሉ። በሜክሲኮ ጓድላሃራ ማራቶን ያለፈው ዓመት የውድድሩ አሸናፊ ኢትዮጵያዊው አትሌት ሙሳ ባቦ ውድድሩን የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት አግኝቷል። በሴቶች አትሌት በላይነሽ ሽፈራው፣ አትሌት ለምለም በርሄና አትሌት ቢሎ ባስናቀ ይሳተፋሉ። በሌላ በኩል በቱርክ ኢንስታንቡል ማራቶን በወንዶች ኢትዮጵያዊው አትሌት ጌቱ ፈለቀ የሚሳተፍ ይሆናል። በአጠቃላይ የማራቶን ውድድሮች በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ደረጃና ዕውቅና የተሰጣቸው ናቸው።