ቀጥታ፡

አባቶች የመከፋፈልና የዘረኝነት አሰተሳሰብን በመለወጥ በኩል ትልቅ ድርሻ አላቸው

አዲስ አበባ ህዳር 1/2011 የቤተ-ክርስቲያን አባቶች ኃላፊነትና ተሰሚነታቸውን በመጠቀም የመከፋፈልና የዘረኝነት አስተሳሰብን ሊቀይሩ እንደሚገባ በአሜሪካና አውሮፓ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያንን የሚያገለግሉ አባቶች ተናገሩ። በውጭና በአገር ውስጥ የነበሩትን ሁለት ሲኖዶሶች አንድ በማድረጉ ስራ ተሳትፎ ሲያደርጉ የነበሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን አባቶች እንዳሉት "የኃይማኖት አባቶች ተሰሚነታችንን በመጠቀም ሕዝቡን ከጥላቻ ንግግርና ከመከፋፈል ለማዳን መስዋዕትነት መክፈል ይገባል"። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ሕዝቡ የሚፈልገው ለውጥ እየመጣ መሆኑንና በተቃራኒው የጥላቻና የመከፋፈል ስሜቶችን የሚያንፀባርቁ አካላትን በማስተማር በኩል ቤተ-ክርስቲያን አስፈላጊ ተግባራትን ልታካሂድ ይገባል ነው ያሉት። በአሜሪካና አውሮፓ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያንን የሚያገለግሉ እነዚሁ አባቶች እንደሚሉት ምእምናን ከጊዜ ወደጊዜ እየታየባቸው ያለውን የመከፋፈልና የጥላቻ አዝማሚያ በመተው ሁሉን በእኩል በማየት እንዲራመዱ መስራት ምርጫ የማይሰጠው ጉዳይ ነው። አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል በካናዳ የተክለሃይማኖት ቤተ-ክርስቲያን አስተዳዳሪና ቀሲስ ዶክተር መዝገቡ ካሳ እንደሚሉት በልዩነት ውስጥ አገርን መገንባትም ሆነ ማሕበራዊ አንድነትን አምጥቶ የሚፈልጉት ደረጃ መድረስ አይቻልም። ''በተለይ በቤተ-ክርስቲያን ሕብረታችን አንድነታችን ነው ይበልጥ ትርጉም ያለው ክርስቲያኖች ከአንድነት ውጭ እነሱን ሊገልጽ የሚችል ምንም አይነት ባሕርይ ወይም አቋም የለም።እንደ ክርስቲያን ማለት ማሕበረሱቡ የቋንቋ ልዩነት ሳይሰማው የሃይማኖት ልዩነት ሳይሰማው ሁሉ ተከባብሮ ተፈቃቅሮ ተደጋግፎ በደስታውም በሀዘኑም አብሮ የሚኖር ሕዝብ ነው ፤ ሰው አንድ ከሚያደርገው ይልቅ የሚያለያየውን ነገር ትኩረት  እያደረገ ወደአልሆነ  አቅጣጫ ነው እየሔደ ያለው ፤ይሕ በእውነቱ ያለመረዳት ካልሆነ በስተቀር እጅግ ሀገራችን ማሕበረሰቡን የሚጎዳ በምንም ተአምር ውጤታማ ሊደርግ የማይችል አካሔድ ነው'' "በመቻቻል ሳይሆን በመፈቃቀርና በመረዳዳት ልንኖር ይገባል" ያሉት ደግሞ በካናዳ የቶሮንቶ ደብረ-ገነት አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ-ክርስቲያን አስተዳዳሪ መላዕከ ህይወት ሀረገወይን ብርሃኑ ናቸው። ''ያለውን አዝማሚያ ቤተ-ክርስቲያን አጥብቃ የምትቃወመው፤ የምትቃወመው ብቻ ሳይሆን በማስተማር ከጥላቻ ፍቅር ፤ከመለያየት አንድነት እንደሚሻል  እንደሚበልጥ እንደሚጠቅም ለይታ በማስተማር ይህንን ችግር የማስወገድ ኃላፊነት ያለባት  ቤተክርስቲያኗ ነች ብዬ አምናለሁ፤ ውስጥ ለውስጥ የመናቆር ነገር ይታያል ሒወት ይጠፋል ንብረት ይወድማል በጠነከረ መንገድ ዘረኝነት ወይም ልዩነቶች ይንፀባረቃሉ ይሔ አደገኛ አዝማሚያ ስለሆነ ቤተክርስቲያን የራሷን መንግስትም የራሱን ሕዝቡም የራሱን አስተዋጽኦ እያደረገ ወደተሻለው አንድነትና መረዳዳት መምጣት ይገባል።'' የሰላም ዋጋው ውድ በመሆኑ በፍቅር መኖርን የመሰለ ነገር የለም የሚሉት ደግሞ በአውሮፓና በስዊድን በስብከት ስራ የተሰማሩት መላዕከ ህይወት ቀሲስ ጌጡ የኋላእሸት ናቸው። እንደ ኃይማኖት አባቶቹ ገለጻ ኢትዮጵያዊያንን የሚያለያዩዋቸው ጥቂት ጉዳዮች ቢኖሩም አንድ የሚያደርጓቸው በርካታ እሴቶች ደግሞ መድመቂያ በመሆናቸው እነርሱን ጠብቆ በፍቅር መኖር ይገባል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም