ጅማ አባ ጅፋርና መከላከያ በአፍሪካ የክለብ ውድድሮች ቅደመ ማጣሪያ ከጅቡቲና ከናይጄሪያ ክለቦች ጋር ይጫወታሉ

43
አዲስ አበባ ህዳር 1/2011 ጅማ አባ ጅፋርና መከላከያ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግና በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ከጅቡቲና ከናይጄሪያ ክለቦች ጋር ይጫወታሉ። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግና የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የቅድመ መጣሪያ ጨዋታዎችን ሙሉ ድልድል ይፋ አድርጓል። በዚሁ መሰረት በ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ የሆነው ጅማ አባ ጅፋር ከጅቡቲው ጅቡቲ ቴሌኮም ጋር ከሁለት ሳምንት በኋላ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደርጋል። ጅማ አባ ጅፋር የመጀመሪያ ጨዋታውን ህዳር 18 ወይም 19 ቀን 2011 ዓ.ም በሜዳው እንደሚያደርግ ሲጠበቅ የመልስ ጨዋታውን ህዳር 25 ወይም 26 ቀን 2011 ዓ.ም በስታድ ዱ ቪል ስታዲየም የሚያደርግ ይሆናል። ጅቡቲ ቴሌኮም ሰባት ጊዜ የጅቡቲ ፕሪሚየር ሊግን ያሸነፈ ሲሆን የጅቡቲ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን ሁለት ጊዜ ማንሳት ችሏል። ጅማ አባ ጅፋር በደርሶ መልስ ጨዋታውን ካሸነፈ ትናንት የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ተፋላሚ ከነበረው አል አሀሊ ጋር በታህሳስ 2011 ዓም ይጫወታል። የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ አሸናፊ በመሆን ኢትዮጵያን በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሚወክለው መከላከያ ከናይጄሪያው ኢኑጉ ሬንጀርስ ጋር የሚጫወት ይሆናል። መከላከያ የመጀመሪያ ጨዋታውን ህዳር 18 ወይም 19 ቀን 2011 ዓ.ም በናምዲ አዚኪዌ ስታዲየም የሚያደርግ ሲሆን የመልስ ጨዋታውን ህዳር 25 ወይም 26 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚያደርግ ይሆናል። መከላከያ የደርሶ መልስ ጨዋታውን ካሸነፈ በታህሳስ 2011 ዓ.ም ከአልጄሪያው ዩኤስኤም ቤል አቤስ ወይም ከላይቤሪያው ኤል አይ ኤስ ሲ አር አሸናፊ ጋር የሚጫወት ይሆናል። በራሪዎቹ ሚዳቆዎቹ የሚል መጠሪያ ያለው ኢኑጉ ሬንጀርስ የናይጄሪያ ፕሪሚየር ሊግን ሰባት ጊዜ የናይጄሪያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን ስድስት ጊዜ ያነሳ ሲሆን የናይጄሪያን አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ አንድ ጊዜ ማሸነፍ ችሏል። በተጨማሪም እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1977 የአፍሪካ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ባለቤት ሆኗል። የዘንድሮው የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ለ55ኛ የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ደግሞ ለ28ኛ ጊዜ የሚካሄድ ይሆናል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም