በክልሉ ሕጻናት ተገቢ ክትባት ባለማግኘታቸው ህብረተሰቡ ገንዘብና ጊዜውን ለሕክምና እያጠፋ ነው

144
አርባምንጭ ግንቦት 15/2010 በደቡብ ክልል ሕጻናት መዳን በሚችሉ በሽታዎች ከመጠቃታቸው በፊት ተገቢ ክትባት ባለማግኘታቸው ሕብረተሰቡ ለፈውስ ሕክምና ገንዘብና ጊዜውን ለማጥፋት እየተገደደ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ። "ክትባት የሕይወት መድህን ነው፤ ሁላችንም የድርሻችንን እንወጣ" በሚል መሪ ቃል 8ኛው የአፍሪካ ክትባት ሳምንት ንቅናቄ በጋሞ ጎፋ ዞን አርባ ምንጭ ከተማ ትናንት ተጀምሯል ፡፡ በደቡብ ክልል ጤና ቢሮ የእናቶችና ሕጻናት ጤናና ስርዓተ ምግብ የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ሽመልስ በንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ላይ እንዳሉት በሕጻናት ክትባት አገልግሎት ላይ የክልሉ አመራር አካላት ሚና ሊጎላ ይገባል። በሚሌኒየም የጤና ልማት ግብ ለክትባት በተሰጠው ተገቢ ትኩረት በክልሉ የሕብረተሰቡ የክትባት አገልግሎት ተጠቃሚነት እያደገ ቢመጣም በተለያየ ምክንያት ክትባት ያልጀመሩና ጀምረው ያቋረጡ በርካታ ሕጻናት አሁንም መኖራቸውንም ገልጸዋል ፡፡ ይህም ህጻናቱ መዳን በሚችሉባቸው በሽታዎች ከመጠቃታቸው በላይ በሕከምና ምክንያት የማህበረሰቡ ጊዜና ገንዘብ እየባከነ መሆኑን አመልክተዋል። ስምንተኛው የአፍሪካ ክትባት ሳምንት ንቀናቄው በመልክአ ምድር አቀማመጥ ፣ በመሠረተ ልማት አለመሟላትና በግንዛቤ እጥረት ምክንያት ክትባት ጀምረው ላቋረጡና ላልጀመሩ ሕጻናት ትኩረት የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ሁሉም የአመራር አካላት አንድም ሕጻን ሳይከተብ እንዳይቀር የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል ፡፡ መደበኛ የክትባት ዘመቻውም እንዳይስተጓጎል በሶላር የሚሠሩ 668 የክትባት ማቆያ ማቀዝቀዣዎች በክልሉ ለሚገኙ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች እንዲሰራጩ መደረጉን አቶ ሽመልስ ተናግረዋል፡፡ በፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የክትባት መርሀ-ግብር ባለሙያ አቶ ጌትነት ባይህ በበኩላቸው በአገሪቱ ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ሕጻናት 11 የክትባት ዓይነቶች እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡ በአገሪቱ ሁሉን አቀፍ የክትባት አገልግሎት ያገኙ ሕጻናት ሽፋን በአሁኑ ወቅት ከ91 በመቶ በላይ  መድረሱን ባለሙያው ገልጸው ፣ ሽፋኑን ከእዚህም በላይ ለማሳደግ የውሳኔ ሰጪ አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ ከትናንት ጀምሮ ለስምንት ተከታታይ ቀናት በሚሰጠው የክትባት ዘመቻ በመደበኛው ክትባት መድረስ ያልተቻሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ይሆናሉ፡፡ በጋሞ ጎፋ ዞን ክትባቱን ጀምረው የሚያቋርጡና ሙሉ በሙሉ የማይከተቡ ሕጻናት መኖራቸውን የገለጹት ደግሞ በዞኑ ጤና መምሪያ የእናቶችና ሕጻናት ስርዓተ ምግብ ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አንበሴ ሳጶ ናቸው ፡፡ ክትባቶች እንዳይበላሹ በነጭ ጋዝ የሚሰሩ ማቀዝቀዣዎች በጥንቃቄ ከመጠቀም አኳያ በዞኑ ከአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ በስተቀር ሌሎች ወረዳዎች ተገቢ በጀት እየመደቡ ባለመሆኑ ማቀዝቀዣዎቹን በአግባቡ እየተጠቀሙበት አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ በክትባት ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ላይ የውሳኔ ሰጪ አመራር አካላት መገኘታቸው በቀጣይ ችግሩን ለመቅረፍ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው በክትባት ሥራው የተለያዩ የሕብረተሰቡ አደረጃጀቶችን መጠቀም ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡ በንቅናቄ መድረኩ ላይ በጋሞ ጎፋ ዞን ከሚገኙ ወረዳዎች የጤና፣ የሴቶችና ሕጻናት፣ የትምህርትና የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ተቋማት ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም