በነገው እለት በሚካሄዱ የሩጫ ውድድሮች ምክንያት ዝግ የሚሆኑ መንገዶች ይፋ ሆኑ - ኢዜአ አማርኛ
በነገው እለት በሚካሄዱ የሩጫ ውድድሮች ምክንያት ዝግ የሚሆኑ መንገዶች ይፋ ሆኑ
አዲስ አበባ ህዳር 1/2011 በነገው እለት በሚካሄዱ የሩጫ ውድድሮች ምክንያት ለተሽክርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶች ይፋ ሆኑ። የኢትዮ-ኤርትራና የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የሩጫ ውድድሮች በነገው እለት በአዲስ አበባ ከተማ ይካሄዳሉ። የኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ፣ የአንድነትና የፍቅር ሩጫ ከመስቀል አደባባይ በመነሳት በግሎባል ሆቴል -አጎና ሲኒማ- ጎተራ -ማሳለጫ- ወሎ ሰፈር- ኦሎምፒያ አድርጎ መስቀል አደባባይ የሚጠናቀቅ ይሆናል። ለውድድሮቹም ፖሊስ በቂ ዝግጅት እንዳደረገና ውድድሩ እስኪጠናቀቅ ድረስም ለተሽከርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶችን ዝርዝር አስታውቋል። ውድድሩ እስኪጠናቀቅ ድረስ ለተሽከርካሪ ዝግ የሚሆኑ ቦታዎችም ከባምቢስ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ፣ከብሄራዊ ቤተመንግስት ወደ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ፣ከሀራምቤ ሆቴል በጋንዲ ሆስፒታል ወደ መስቀል አደባባይ፣ከሳሪስ ወንጌላዊት ህንጻ ወደ ወሎ ሰፈር የሚወስዱ መንገዶች ዝግ የሚሆኑ ናቸው። ከጎተራ ወደ ወሎ ሰፈርና ከጎተራ ወደ መስቀል አደባባይ ለተሽካካሪዎች ዝግ ናቸው። እንዲሁም ከሜክስኮ አደባባይ ወደ ለገሀርና ከቦሌ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስዱ መንገዶችም ለትራፊክ ዝግ የሚሆኑ ይሆናሉ ተብሏል። በእነዚህ ቦታዎች የሚሄዱ አሽከርካሪዎች በአማራጭነት መጠቀም የሚቻልባቸው ቦታዎች የተገለጹ ሲሆን ከመገናኛ ወደ አራት ኪሎ የሚሄዱ አሽከርካሪዎች በኡራኤል አድርገው በካሳንቺስ ወደ አራት ኪሎ መጠቀም ይችላሉ ተብሏል። ከመገናኛ ወደ ጦር ኃይሎች የሚሄዱ ተሽክካሪዎች ደግሞ በኡራኤል- ካሳንቺስ-ሂልተን ሆቴል-ፍልውሃ-ብሄራዊ-ትያትር-ሜክስኮ አደባባይ አድርገው በልደታ ጦር ኃይሎች መሄድ የሚችሉ ይሆናል። ተሳታፊ ስፖርተኞችም ወደ ውድድሩ ሲመጡ ስለታም የሆኑና የጦር መሳሪያን ይዞ መግባት እንደማይቻል ፖሊስ አስታውቋል። ህብረተሰቡም ለፀጥታ አጠራጣሪ የሆኑ ነገሮችን ከተመለከተ በስልክ ቁጥር 011-5-52-63-03 / 011-5-52-40-77 / 011-1-01-11 ወይም በነጻ ስልክ መስመር 991 አልያም 987 ማሳወቅ እንደሚችሉ ገልጿል።