ቀጥታ፡

አምባሳደር አድማሱ ፀጋዬ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለማሌዥያ ንጉስ ተወካይ አቀረቡ

አዲስ አበባ ህዳር 1/2011 በኢንዶኔዥያ፣ሲንጋፖርና ማሌዥያ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ፕሮፌሰር አድማሱ ፀጋዬ ለማሌዥያው ንጉስ ተወካይ ሱልጣን ናዚን ሙዘይዲን የሹመት ደብዳቤያቸውን አቀረቡ፡፡ ሱልጣኑም ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሆነው በመመረጣቸው የተሰማቸውን ደስታ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ አስታውቋል። አምባሳደር አድማሱ፣ ተቀማጭነታቸው በኢንዶኔዥያ ጃካርታ እንደሆነ ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ኢትዮጵያና ማሌዥያ ዋነኛ የሁለትዮሽ ትብብራቸው ያተኮረው ከዲፕሎማሲ ይልቅ በኢኮኖሚ ትስስር የተመሰረተ ነው። ኢትዮጵያ በማሌዥያ ርዕሰ መዲና ኩዋላላምፑር እ.አ.አ በ2003 የቆንጽላ ጽህፈት ቤት የከፈተች ሲሆን በአንጻሩ ማሌዥያ በኢትዮጵያ ኤምባሲም ሆነ የቆንጽላ ጽህፈት ቤት የላትም። ማሌዥያ ዋነኛ የኢትዮጵያ የንግድ አጋር ከሚባሉ አገራት የምትጠቀስ ሲሆን ባለሃብቶቿ በነዳጅ ፍለጋና ምርት እንዲሁም በምግብ ዘይት በኢትዮጵያ ኢንቨስት እያደረጉ ነው።                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም