ቀጥታ፡

የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት በተሟላና ተገልጋይን በማያጉላላ ፍጥነት እየተሰጠ ነው-ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል

አዲስ አበባ   ህዳር 1/2011 ኢትዮጵያ መስጠት የጀመረችው የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት በተሟላና ተገልጋይን በማያጉላላ ፍጥነት እየተሰጠ መሆኑ ተገለጸ። አንድ ተገልጋይ ወደ መዳረሻ ቪዛ አገልግሎት መስጫ መስኮቶች ካቀናም በሰኮንዶች አገልግሎቱን አግኝቶ እንደሚሄድ ነው የተገጸው። የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚልና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ ትናንት ማምሻውን በኢትዮጵያ አየር መንግድ ተገኝተው የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት አሰጣጥ ሂደትን ጎብኝተዋል። ከጉብኝቱ በኋላ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት እንደገለጹት፤ "የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎትን ለመጀመር የተደረው ዝግጅት የሚደነቅ ነው፤ ገና ከጅምሩ እየተሰጠ ያለው አገልግሎት ፈጣንና ቀልጣፋ መሆኑም ደስ የሚያሰኝ ነው"። ከደህንነት አንጻርም አስጊ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን በቀላሉ መለየትና መቆጣጠር የሚቻልበት ዘዴ መመቻቸቱንና በቂ ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል። ''የአገልግሎቱ መጀመር አገሪቷ ከሌሎች አገራት ጋር ያላትን ትስስር የበለጠ የሚያጠናክርና የአገር ገጽታ ከሚገነባባቸው ስራዎችም አንዱ በመሆኑ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት'' ሲሉም ተደምጠዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂሩት ዘመነ በበኩላቸው ይህ ተግባር እንደ አውሮፓዊያን የዘመን ቀመር 2063 አፍሪካ አህጉራዊና ቀጠናዊ ትስስርን ለማሳለጥና የሰውንና የዕቃ ዝውውር ነጻ ለማድረግና ለማቀላጠፍ የተያዘው እቅድ አካል መሆኑን አስረድተዋል። ኢትዮጵያም እንደ አፍሪካ ኀብረት መስራችና መቀመጫነት የመዳረሻ ቪዛ መጀመሯ ለሌሎች  ምሳሌ የሚሆን ተግባር ነው ብለዋል። እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ ኢትዮጵያ ወንድም አፍሪካዊያንን ለመቀበልና በሁሉም ዘርፍ ለመዋሃድ ያላትን ዝግጁነትንም የሚያሳይ ስራ ነው። ከዚያም በተጨማሪ አገሪቷ ብዙ የቱሪስት መዳረሻ ያለት እንደመሆኗ ከዚህ አገልግሎት ብዙ ትጠቀማለች ሲሉም አብራርተዋል። በኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢሚግሬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ አይክፋው ጎሳዬ በበኩላቸው አገልግሎቱን በበቂ ሁኔታ ለመስጠት የሚያስችል የሰው ኃይል፣ ግብዓት ተደራጅቶ ወደ ስራ መገባቱንና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ነው የተናገሩት። በመሆኑም አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ መስኮቶቹ የሚመጣ እንግዳ ከአንድ ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ መግባት የሚያችለውን ቪዛ ማግኘት ይችላል ብለዋል። ኢትዮጵያ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ለሚመጡ ዜጎች የመዳረሻ ቪዛ መስጠት ከጀመረች 10 ቀናት አልፏታል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም