ሶስቱ አገሮች በጠንካራ ኢኮኖሚ የተሳሰረ ማህበረሰብ ለመፍጠር እየሰሩ መሆናቸው ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ሶስቱ አገሮች በጠንካራ ኢኮኖሚ የተሳሰረ ማህበረሰብ ለመፍጠር እየሰሩ መሆናቸው ተገለጸ
ጎንደር ህዳር 1/2011 በምስራቅ አፍሪካ በጠንካራ ኢኮኖሚ የተሳሰረ ማህበረሰብ ለመፍጠር ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን የሶማሊያ ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ ገለጹ። በአማራ ብሄራዊ ክልል ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ በማዕከላዊ ጐንደር ዞን በምዕራብና ምስራቅ ደንቢያ ወረዳዎች የሚገኘውን የመገጭ ስረባ የመስኖ ኘሮጀክትን ጐብኝተዋል። ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ በጦርነት የሚታወቁበት ወቅት አልፎ በጠንካራ ኢኮኖሚ ለመተሳሰር በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ። ሶስቱ አገሮች በምስራቅ አፍሪካ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለመፍጠር በተለያዩ መስኮች ላይ ትኩረት አድርገው እየሰሩ መሆኑን ነው አጽንኦት የሰጡት። የሁለቱ ፕሬዚዳንቶች የኢትዮጵያ ጉብኝትም ዓላማ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም ላይ አዎንታዊ ተፅእኖ እየፈጠረ የሚገኘው የለውጥ ሂደትና የምጣኔ ኃብታዊ ትብብርን ለማመቻቸት የሚካሄደውን እንቅስቃሴን ለማጠናከር መሆኑ ነው የተነገረው። ጉብኝቱ ባለፈው ወር በኤርትራ አስመራ የተካሄደው የሶስቱ አገሮቹ የጋራ ምክክር ተከታይና በአገሮቹ መካከል የተጀመረውን ውይይት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ያለመ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በወቅቱ እንደገለጹት፤ አገሮቹ ለራሳቸው የሚበቁና ለሌሎች የሚተርፉ ናቸው። ስለዚህ ወጣቶች ይህን በመገንዘብ መማር፣ ማስተዋልና ነገሮችን በጥሞና መመልከት ይኖርባቸዋል። ወጣቶች የሚመኙትን ትልቅ አገር ለመፍጠር፣ ለመምራት፣ ለመስራትና ለማገልገል ሙሉ ጊዜያቸውን በትምህርትና በምርምር ሊያውሉ እንደሚገባም ተናግረዋል። እንዲሁም ምስራቅ አፍሪካን አንድ ለማድረግ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ወጣቶች እንዲበረቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጥሪ አቅርበዋል። በተመሳሳይ የሦስቱ አገሮች መሪዎች ግንባታው በመካሄድ ላይ የሚገኘውን የቡሬ አግሮ ኘሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጐብኝተዋል። የአግሮ ኘሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኩ 260 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ 5ዐ በመቶ ተጠናቋል። የፓርኩ ግንባታ ሲጠናቀቅ የቡሬ ከተማና የአካባቢው አርሶ አደር ተጠቃሚ ያደርጋል።