ቀጥታ፡

የጋምቤላ ከተማ የልማትና የመልካም አስተዳደር ፕሮጀክት ፀደቀ

ጋምቤላ ጥቅምት 30/2011 የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ምከር ቤት ትናንት ባከሄደው ስድስተኛ አስቸኳይ ጉባዔ በከተማው የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ የልማት ፕሮጀክት አጸደቀ። በምክር ቤቱ የጸደቀው ፕሮጀክት በከተማው የሚታዩ የመሠረተ ልማት ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ፣ ለዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራል ተብሏል። ፕሮጀክቶቹ በመንገድ፣ በጎርፍ ማፋሰሻ ቱቦዎች፣ በመጸዳጃ ቤቶች ግንባታ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ላይ ያተኩራሉ። ''የከተማ ተቋማዊ መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክት'' የሚል መጠሪያ የተሰጠው ፕሮጀክት ለአምስት ዓመታት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን፣ ከዓለም ባንክ፣ ከጋምቤላ ከተማ አስተዳደርና ከኅብረተሰቡ በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ይተገበራል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመትም ከ60 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የስድስት የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ መንገዶች፣ የተለያዩ የጎርፍ ማፋሰሻ ቦዮች ግንባታ፣ የመንገድ ላይ መብራት ዝርጋታና የነባር መንገዶች ጥገና ይከናወናሉ። ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አቶ አካኒ ኦፖዶ በሰጡት አስተያየት በከተማው ሊተገበር የታቀደው ፕሮጀክት ህዝብ በብዛት ባለባቸው አካባቢዎችና የህዝቡን መሠረታዊ ችግሮች ባገናዘበ መልኩ ሊሆን  ይገባል ብለዋል። ከአሁን በፊት የተሰሩት መንገድ፣ የውሃ ማፋሰሻና ሌሎች ግንባታዎች የጥራት ጉድለት እንደነበረባቸው አስታውሰው፣ በአዲሱ ፕሮጀክት ተመሳሰይ ችግር እንዳይከሰት ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ  የምክር ቤቱ አባል አቶ ዳንኤል ወንድሙ አሳስበዋል። ሌለው የምክር ቤት አባል አቶ ኡቻን ባሮ በሰጡት አስተያየት በማፋሰሻ ቱቦዎች ችግር በከተማው በተደጋገሚ እየተከሰተ ያለው የጎርፍ አደጋ በአዲሱ ፕሮጀክት መፍትሄ መስጠት እንደሚያስፈለግ ተናግረዋል። የከተማው ከንቲባ አቶ ቺቢ ቺቢ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ የከተማውን ሁለንተናዊ እድገትና የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ተናግረዋል። አስተዳደሩ ፕሮጀክቱን በጥራትና በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ በመፈጸም የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ  እንደሚሰራም አስታውቀዋል። የፕሮጀክቱ አስተባበሪ አቶ ትዕግስቱ በፍቃዱ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የከተማውን የመሠረተ ልማት ችግሮች እንደሚፈታና ለዜጎች ሥራ  እንዲፈጥር ታልሞ የተቀረጸ ነው ብለዋል። በፕሮጀክቱ በየዓመቱ ከ 2ሺህ 500 ለማያንሱ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ ሥራ ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም