ኢትዮጵያ በሴቶች የአመራርና የውሳኔ ሰጪነት ተሳትፎ አስደናቂ ለውጥ እያስመዘገበች ነው---የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሴቶች የአመራርና የውሳኔ ሰጪነት ተሳትፎ አስደናቂ ለውጥ እያስመዘገበች ነው---የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር
መቀሌ ጥቅምት 30/2011 ኢትዮጵያ የጾታ እኩልነትና የሴቶችን ውሳኔ ሰጪነት በማሳደግ ረገድ አስደናቂ የለውጥ እያስመዘገበች መሆኑን የኢፌዴሪ የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ወልደማሪያም አስታወቁ። የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀው የሴት ምሁራን ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ዛሬ በዩኒቨርሲቲው ዋና ጊቢ ተጀምሯል። ሚኒስትሯ በመክፈቻው ላይ እንዳሉት፣ሴት ምሁራን በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣በፈጠራ ስራና በውሳኔ ሰጭነት ከፍተኛ ቦታ ላይ ተሳትፏቸው እንዲጎለብት የሁሉንም ጥረት ይጠይቃል። "የጾታ እኩልነት መረጋገጥ ለሃገር ልማት ግንባታ፣ለዘላቂ ልማት መረጋገጥና ብሎም ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ወሳኝ ነው" ያሉት ዶክተር ሂሩት ሴቶች በዘርፎቹ እንዲሳተፉ ራሳቸውን ማዘጋጀት እንዳለባቸው ተናግረዋል። ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት የስርዓተ ጾታ እኩልነትን እውን ማድረጉን ገልጸው “ለውጡ በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ በተግባር ሊታይ ይገባል”ብለዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ በፕሮፌሰርነት ደረጃ የሚገኙት ሴቶች ቁጥር አነስተኛ ከመሆኑም ባሻገር ሃገሪቱ ካሏት 50 ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በ18ቱ ብቻ ምክትል ፕሬዝዳንቶች መገኘታቸው በዘርፉ ያላቸውን ዝቅተኛ ተሳትፎ እንደሚያሳይ አመልክተዋል። በርካታ ሴት ምሁራን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ በዝቅተኛ የሃላፊነት ቦታ ላይ ይገኛሉ ያሉት ዶክተር ሂሩት፣”ሴት አትችልም ከሚለው የተሳሳተ ድምዳሜና ፍረጃ ወጥተን ሴቶችን ማብቃት ይጠበቅብናል” ብለዋል። ለዚህ ስኬት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተለይም ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በቀጣይ ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም የሴቶችን ሁለንናዊ ተሳትፎ በተለይም በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣በፈጠራ ስራ፣በሳይንስና ልማት ዘርፎች ላይ የላቀ ድርሻ እንዲኖራቸው ማነሳሳት፣ማብቃትና ማስተማር ላይ እንደሚሰራ ጠቁመዋል። “ዛሬ ላይ 50 በመቶ ያህል የፌዴራል መንግስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በሴቶች እንዲመሩ ተደርጓል፣በተለይም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የሃገር መከላከያና የሰላም ሚኒስቴሮች በሴት እንዲመሩ መደረጉ ለውጡ እጅግ አስደናቂና ታሪካዊ ነው” ብለዋል። ‘‘ሴቶች የከፍተኛ ትምህርት ፕሪዚዳንቶች፣ሳይንቲስቶች፣ፕሮፌሰሮች መሆን እንችላልን እንፈልጋልን‘‘ በማለት ራሳቸውን ማዘጋጀት ይገባቸዋል ብለዋል። የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት በበኩላቸው እንደተናገሩት ለዓመታት ምላሽ ሳያገኝ የቆየው የሴቶች የጾታ እኩልነት ጥያቄ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምላሽ ማግኘት ጀምሯል። የሴቶችን የአመራር ተሳትፎ ለማሳደግ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በርካታ ጥረቶች ሲያከናውን መቆየቱን ያመለከቱት ፕሬዚዳንቱ፣የሴት ምሁራንን ተሳትፎ ለማሳደግ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ 560 ሴት መምህራንን ቅጥር ማካሄዱን ተናግረዋል። “ሴት ተመራማሪዎችን ለማነሳሳት የሴት ተመራማሪዎች ፈንድ፣የሴት ተማሪዎች ህብረት ተቋቁመው መልካም ስራዎችን እየሰሩ ነው” ብለዋል። ሴት ምሁራን በፈጠራ ስራ፣በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣በአመራር ሰጭነትና በልማት ዘርፎች ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማነሳሳትም ዩኒቨርሲቲው ከመቸውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል። ዛሬ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በተጀመረው ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ላይ አምስት ሴት ሚኒስትሮችን ጨምሮ ከ500 በላይ በኢትዮጵያ ከሚገኙ 44 መንግስታዊ ዩኒቨርስቲዎች ተወካዮች፣ከአፍረካና አውሮፓ ሃገራት የተወከሉ ሴት ምሁራን ተገኝተዋል። በኮንፈረሱ የሁለት ቀናት ቆይታ ላይ በርካታ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ይካሄድባቸዋል።