ቀጥታ፡

የዞኑ ሰላም እየተመለሰ ነው

ባህርዳር ጥቅምት 30/2011 በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን  ተፈጥሮ  የነበረው አለመረጋጋት ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እየተመለሰ መሆኑን  የክልሉ ሰላምና ደህንነት ቢሮ አስታወቀ። እየተገባደደ ካለው ሳምንት መግቢያ ጀምሮ በአካባቢው ተከስቶ የነበረው  አለመረጋጋት ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ የተመለሰው ህዝቡና የፀጥታ አካላት  ባደረጉት የተቀናጀ  ጥረት ነው፡፡ የቢሮው ኃላፊ ብርጋዴል ጀኔራል አሳምነው ፅጌ ለኢዜአ እንደገለጹት አሁን በተፈጠረው አንፃራዊ ሰላም በተለይም በዞኑ ገንዳ ውሃ ከተማና አካባቢው ስራ አቁመው የነበሩ ሱቆችና የትራንስፖርት አገልግሎት መደበኛ ስራቸውን ጀምረዋል። ከመከላከያ፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከክልሉ ልዩ ኃይልና ከአካባቢው የጸጥታ አካል የተውጣጣ ኮሚቴ ተዋቅሮ የአካባቢውን ሰላም የማስጠበቅ  ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡ ተፈጥሮ በነበረው ችግር በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ያመለከቱት የቢሮው ኃላፊ  ከአንድ ሺህ 400 የሚበልጡ ነዋሪዎች  መፈናቀላቸውን  አስታውቀዋል። የችግሩ መንስኤ የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚፈልጉ ኃይሎች በፈጠሩት ሴራ እንደሆነ ጠቁመው  የቅማንትና የአማራ ህዝቦች ለዓመታት አብረው የኖሩ፣ ከልዩነት ይልቅ አንድነታቸው የጎላ ፣በዕምነት፣ በቋንቋ፣ በስነ-ልቦናና በባህል አንዱን ከሌላው መለየት እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ኃይሎችም በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር በሰው ኃይል፣ በስልጠና፣ በቁሳቁስና በሌላም ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነ ማወቅ እንደተቻለም አብራርተዋል። አካባቢውን የግጭት ቀጠና ለማድረግም ህገወጥ የጦር መሳሪያ ወደ ክልሉ በብዛት እንደሚገባ ገልጸው፤ በቅርቡም በተለያየ ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ መሳሪያዎች መያዛቸውን  አስረድተዋል። ችግሩ በተፈጠረባቸው አካባቢዎች ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት በትኩረት እንደሚሰራ የገለጹት ኃላፊው የአካባቢው ማህበረሰብ በድርጊቱ ተሳታፊ ከመሆን ተቆጥቦ ለሰላምና መረጋጋት ተባብሮ ሊሰራ እንደሚገባው አሳስበዋል። የአካባቢው የሃገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶችና ምሁራን የተፈጠረው ችግር ባለበት እንዲቆም ምክረ ሃሳብ በማቅረብ የበኩላቸውን እንዲወጡም ብርጋዴል ጀኔራል አሳምነው ጥሪ አቅረበዋል። ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች እየተያዙ መሆኑንና  ጉዳያቸው ተጣርቶ በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም