ቀጥታ፡

የውሹ የአሰልጣኝነት ደረጃ ማሻሻያ ፈተና የወሰዱት አብዛኞቹ አሰልጣኞች ፈተናውን አላለፉም

አዲስ አበባ ጥቅምት 30/2011 የውሹ የአሰልጣኝነት ደረጃ ማሻሸያ ፈተና የወሰዱት አብዛኞቹ አሰልጣኞች ፈተናውን አላለፉም። ከጥቅምት 26 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ የውሹ የአሰልጣኝነት ደረጃን ለማሻሻል ሲሰጥ የነበረው የፈተና መርሃ ግብር ዛሬ ተጠናቋል። በፈተናው በሁለቱም ጾታዎች ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 209 አሰልጣኞች ተሳትፈዋል። የኢትዮጵያ ውሹ ፌዴሬሽን የውድድርና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ገበየሁ ሙሉጌታ ለኢዜአ እንደገለጹት የጽሁፍና የተግባር ፈተናው የተሰጠው ደረጃቸውን ከአንድ እስከ ሶስተኛ ዳን ማሻሻል ለሚፈልጉ አሰልጣኞች ነው። በዚሁ መሰረት ፈተናውን ከወሰዱት አሰልጣኞች 53ቱ ብቻ ደረጃቸውን ማሻሻላቸውንና የተቀሩት 156 አሰልጣኞች ፈተናውን ማለፍ አለመቻላቸውን ተናግረዋል። የኢዜአ ሪፖርተር አብዛኞቹ አሰልጣኞች ለምን ፈተናውን አላለፉም? ምክንያቱ ምንድን ነው? በሚል ላነሳው ጥያቄ አቶ ገበየሁ "አሰልጣኞቹ ራሳቸውን በማብቃት ስፖርቱ አሁን ከደረሰበት ደረጃ ጋር ማሳደግና ማሻሻል ባለመቻላቸው ነው" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። የውሹ ፌዴሬሽን አሰልጣኞች አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ስልጠና እንደሚሰጥ ገልጸው ያም ቢሆን አሰልጣኞች በግላቸው ራሳቸውን ማሻሻልና በስፖርቱ ውስጥ የሚጨመሩ አዳዲስ ነገሮችን ማወቅ እንደሚገባቸው ገልጸዋል። አሰልጣኞቹም ለስፖርቱ የሚሰጡት ትኩረት ዝቅተኛ መሆንና ወጥነት ባለው መልኩ ለስፖርቱ ያላቸው ቁርጠኝነትና ፍላጎት የሚጠበቀውን ያህል እንዳልሆነም አስረድተዋል። በፈተናው 30 አሰልጣኞች ከጥቁር ቀበቶ ወደ አንደኛ ዳን፤ 15 አሰልጣኞች ከአንደኛ ወደ ሁለተኛ ዳን የተቀሩት ስምንቱ ደረጃቸውን ከሁለተኛ ወደ ሶስተኛ ዳን ደረጃቸውን ማሻሻላቸውን ነው አቶ ገበየሁ ያብራሩት። ከፈተናው በፊት ስልጠና የሚሰጥ ሲሆን ፈተናውን በብቃት የሚወጡ አሰልጣኞችም ባሉበት አካዳሚ የውሹ ስፖርት ማዕከላትን በመክፈት ስፖርተኞችን የማሰልጠን ፈቃድ እንደሚያገኙ አመልክተዋል። በፈተናው ላይ ሁሉም ክልሎች እንዲሳተፉ ጥሪ መቅረቡንና ከጋምቤላና አፋር ክልሎች በስተቀርም ሁሉም  ክልሎች ተሳታፊዎችን ልከው ፈተናውን እንደወሰዱ ጠቅሰዋል። በፈተናም ደረጃቸውን ያሻሻሉት አሰልጣኞች ባሉበት አካዳሚ የውሹ ስፖርት ማዕከላትን በመክፈት ስፖርተኞችን የማሰልጠን ፈቃድ እንደሚያገኙና ይህም ብቁና ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እንደሚያግዝ አክለዋል። በአጠቃላይ ፈተናውን ላለፉት አሰልጣኞች የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እንደተሰጣቸውም ገልጸዋል። በተያዘው በጀት ዓመት የአሰልጣኝነትና የዳኝነት ስልጠና እንዲሁም የዳን ደረጃ ፈተና ለመስጠት በእቅድ መያዙንም ጠቁመዋል። የአምስተኛ ዳን ደረጃ ያላቸው ማስተር አህመድ አብዱልቃድር፣ ማስተር ተሾመ አባተ፣ ማስተር ቶፊቅ ሹሜና ማስተር ከበደ ገብሬ ፈተናውን ለአሰልጣኞች ሰጥተዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የውሹ ስፖርት ትልቁ የአሰልጣኝነት ደረጃ ዘጠነኛ ዳን የሚባለው እንደሆነ የዓለም አቀፉ የውሹ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም