አቅሙን ለማሳደግና ሁሉን አቀፍ ለመሆን የሚያስችል ሪፎርም እንደሚያደርግ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
አቅሙን ለማሳደግና ሁሉን አቀፍ ለመሆን የሚያስችል ሪፎርም እንደሚያደርግ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ
አዲስ አበባ ጥቅምት 30/2011 አቅሙን ለማሳደግና ሁሉን አቀፍ ለመሆን የሚያስችል ሪፎርም እንደሚያደርግ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ። የጋራ ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ የቆመለትን ዓላማ ማሳካት አለመቻሉን ገምግሟል። የጋራ ምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎች በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከመወያየት ይልቅ የግል ጉዳይ በምክር ቤቱ እየተነሳ የሚደረጉ ስብሰባዎች በጭቅጭቅና ንትርክ እንደሚባክኑም የጋራ ምክር ቤቱ ገምግሟል። የምክር ቤቱ መቋቋሚያ አዋጅ 662/2002 ብዙ የማያሰሩና ሌሎች መቀላቀል ለሚፈልጉ ፓርቲዎችም በር የሚዘጉ አንቀፆች አሉበት የሚሉ ሀሳቦችም በስብሰባው ተነስተዋል። በአጠቃላይ በአገሪቷ እየመጣ ያለውን የፖለቲካ ለውጥና አስተሳሰብ የሚመጥንና አባል ያልሆኑ ፓርቲዎችን ለማቀፍ የሚያስችል ጠንካራ ሪፎርም ለማድረግ የሚያስገድደው መሆኑን የጋራ ምክር ቤቱ ከስምምነት ደርሰዋል። በዚህ መሰረት የጋራ ምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎች የማሻሸያ ሀሳቦችን ለጋራ መክር ቤቱ ፅህፈት ቤት አቅርበው በቀጣይ በሚካሄድ ስብሰባ ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘዋል። ከዚህ በተጨማሪ የጋራ ምክር ቤቱ ፅህፈት ቤቱ ራሱን የቻለና የተደራጀ ለማድረግ መንግስት ባለሙያዎችን ከመመደብ ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑ የገዢው ፓርቲ ተወካይ አስረድተዋል። የጋራ ምክር ቤቱ በዛሬው ዕለት ባካሄደው ስብሰባ ሌሎች ተጨማሪ ጉዳዮችንም አንስቶ ተወያይቷል። ለአብነትም የጋራ ምክር ቤቱ አባል ለመሆን ከሁለት ፓርቲዎች የቀረበለተን ጥያቄ አፅድቀዋል። በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ኮንግረስ (ኮንግረስ) እና የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት (መአህድ) የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል ሆነዋል። ሁለቱ ፓርቲዎችን ጨምሮ የጋራ ምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎች ቁጥር ወደ 16 ከፍ ብለዋል፡፡