ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ማሌዥያ የኢኮኖሚ ትብብራቸውን ለማስፋት ተስማሙ

አዲስ አበባ ጥቅምት 30/2/2011 ኢትዮጵያና ማሌዥያ ሁለገብ የኢኮኖሚ ትብብራቸውን ለማስፋት ተስማሙ፡፡ በኢንዶኔዥያ የኢትዮጵያ ባለ-ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፕሮፌሰር አድማሱ ፀጋዬ በማሌዥያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ኃላፊ አብዱል ራሽድ ጋር ተወያይተዋል፡፡ በዚህ ወቅትም የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገርና በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በቱሪዝም መስኮች አገራቱ ያላቸውን ትብብር ለማጎልበት ተስማምተዋል፡፡ አምባሳደሩ በኢትዮጵያ ብሎም በምስራቅ አፍሪካ ስላለው ወቅታዊ የሰላምና የወዳጅነት ሁኔታ ለረዳት ኃላፊው ገለፃ አድርገዋል፡፡ በተጨማሪም አምባሳደሩ በማሌዥያ አዲስ ከተሾሙት የኢትዮጵያ የክብር ቆንስል ዳቶ ጃማሉዲን ጋር በኢትዮጵያና በማሌዥያ መካከል ጠንካራና ሁለገብ ትብብር እንዲኖር ለማድረግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መክረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ኢንዶኔዥያ፣ ማሌዥያና ሲንጋፖርን ኢንዶኔዥያ ጃካርታ በሚገኘው ኤምባሲዋ አማካኝነት ነው የምትሸፍነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የሳዑዲ አረቢያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል። በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ባለ-ሙሉ ስልጣን አምባሳደር እና ልዩ መልእክተኛ አብዱልአዚዝ አህመድ በሳዑዲ አረቢያ ከሚገኝ አል-ሳፍዋ እና ፕላምቤክ ሳዑዲ የተሰኘ ኩባንያ ሃላፊዎች ጋር በኢትዮጵያ ባሉት የኢንቨስትመንት እድሎች ዙሪያ ተወያይተዋል። ኩባንያው በግንባታ፣ ሪል ስቴት፣ የታዳሽ ኃይል አቅርቦት፣ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ እና ሌሎች የመሰረተ ልማት ዘርፎች መሰማራት እንደሚፈልግ ገልጿል። አምባሳደር አብዱልአዚዝ እንዳሉት መንግስት፣ ኢትዮጵያ ትኩረት በምትሰጥባቸው የአረንጓዴ ልማትና መሰረተ ልማት መስኮች እንዲሁም የታዳሽ ኃይል ለማመንጨት በሚያስችሉ ዘርፎች ላይ ለሚሰማሩ የውጭ ባለሀብቶችን ያበረታታል። በመሆኑም ኩባንያው በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል። ኢትዮጵያና ሳዑዲ አረቢያ ረጅም ዓመታት ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፤ የአገሪቱ ባለሀብቶችም በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት፣ ንግድ እና የትምህርት መስኮች ተሰማርተው ይገኛሉ። መረጃውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያደረሰው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም