ቀጥታ፡

ምርት ገበያው በጥቅምት ወር 35 ሺህ ቶን ምርት አገበያየ

አዲስ አበባ  ጥቅምት 30/2011 የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በጥቅምት ወር 35 ሺህ ቶን ምርት ማገበያየቱን አስታወቀ። ምርት ገበያው ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በተጠናቀቀው የጥቅምት ወር በተካሔደ ግብይት ካለፈው ወር ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በተለይ በቡና ግብይት በመጠንና በዋጋ ጭማሪ ታይቷል። በዚሁ ወቅት ቡና የግብይቱን በ72 ነጥብ 6 በመቶ በመጠን ደግሞ 83 ነጥብ 9 በመቶ በመያዝ ከፍተኛውን ድርሻ ይዞ እንደነበር አስታውቋል። የቡና የግብይት መጠኑ ካለፈው ወር ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በመጠን በ74 በመቶ በዋጋ ደግሞ በ76 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንም ገልጿል። በአጠቃላይ በዚህ ወቅት 25 ሺህ 577 ቶን ቡና፣ 7 ሺህ 480 ቶን ሰሊጥ እና 2 ሺህ 165 ቶን ነጭ ቦሎቄ ወደ ምርት ገበያው ቀርቦ በ 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መገበያየቱ ነው የተገለፀው። በዚሁ ወር 7 ሺህ 480 ቶን ሰሊጥ በ318 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የተገበያየ ሲሆን የሁመራ ጎንደር ሰሊጥ በግብይት መጠን 73 በመቶ በዋጋ ደግሞ 76 በመቶውን በመያዘ ከሰሊጥ አንደኛውን ደረጃ ይዟል። ይሕም ከባለፈው ወር ተመሳሳይ ግብይት ጋር ሲነፃፀርም በዋጋ በ244 በመቶ እንዲሁም በመጠን በ263 በመቶ ማደጉን ነው ምርት ገበያው ያመለከተው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም