በምዕራብ ሸዋ ዞን ግንባታቸው የተጠናቀቁ ስድስት የጤና ተቋም ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት እየተዘጋጁ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ሸዋ ዞን ግንባታቸው የተጠናቀቁ ስድስት የጤና ተቋም ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት እየተዘጋጁ ነው
አምቦ ጥቅምት 30/2011 በምዕራብ ሸዋ ዞን ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ግንባታቸው በመካሄድ ላይ ካሉ የጤና ተቋም ፕሮጀክቶች መካከል ስድስቱ መጠናቀቃቸውን የዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አበበ ጨመዳ እንዳሉት ከ2008 ዓ.ም ወዲህ ግንባታቸው በመካሄድ ላይ ከነበሩት ሃያ የጤና ተቋም ፕሮጀክቶች መካከል የስድስቱ ግንባታ ተጠናቋል ። "የጊንጪ ከተማ ሆስፒታልን ጨምሮ የአቡና ግንደበረት፣ ኤጀሬ፣ ሊበን ጃዊ፣ የጀልዱና የባኮ ወረዳ ጤና ጣቢያዎች ግንባታ ሥራ በቅርቡ ተጠናቆ ለአገልግሎት ተዘጋጅተዋል" ብለዋል። አቶ አበባ እንዳሉት ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት የተዘጋጁት የተጤና ተቋማት በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ሥራ እንዲጀምሩ በቁሳቁስና በሰው ኃይል የማደራጀት ሥራ እየተካሄደ ነው። ከእዚህ በተጨማሪ በሌሎች አምስት ወረዳዎች ለሚገኙ ጤና ጣቢያዎች የቀዶ ሕክምና መስጫ ህንጻዎች ግንባታ ሥራ እየተፋጠነ መሆኑን ነው የገለጹት። የሌሎች አምስት የጤና ፕሮጀከቶች ሥራም በአማካይ ከ45 እስከ 80 በመቶ መከናወኑን የገለጹት ኃላፊው ቀሪ ሥራዎቹ እስከ በጀት ዓመቱ ሦስተኛ ሩብ ዓመት ድረስ ይጠናቀቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል። እንደ አቶ አበበ ገለጻ የተጠናቀቁትና ግንባታቸው በሂደት ላይ የሚገኙት የጤና ተቋማት ለአገልግሎት ሲበቁ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጥ ህዝብን ተጠቃሚ ያደርጋሉ። በዞኑ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በተያዘው ዓመት ከ36 ነጠብ 8 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ 17 አዳዲስ የጤና ፕሮጀክቶችና የማስፋፊያ ግንባታ ሥራ መጀመሩንም ኃላፊው ገልጸዋል። በአምቦ ወረዳ ሜጢ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ የሆኑት አቶ ታየ በርሲሳ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት ጤና ጣቢያ በአቅራቢያቸው መገንባቱ ከዚህ ቀደም ህክምና ፍለጋ ወደ አምቦ ከተማ የሚሄዱትን ጉዞ እንደሚያስቀር ተናግረዋል። ሌላዋ የእዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አይናለም ፈይሳ በተለይ በወሊድ ጊዜ ህክምና ፍለጋ ከአካባቢ ርቆ ሲኬድ በህጻናትና በእናቶች ላይ ይደርስ የነበረውን ጉዳት እንደሚያስቀርላቸው ነው የገለጹት ። "በአካባቢያችን ቀዶ ህክምና የሚሰጥ ተቋም ባለመኖሩ ከእዚህ ቀደም ወንድሜ ትርፍ አንጀት ሲታመም ህክምና ፍለጋ ወደአዲስ አበባ ለመምጣት ተገደን ነበር" ያሉት ደግሞ የአጄሬ ከተማ ነዋሪ አቶ በላቸው ነገሪ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአካባቢያቸው የቀዶ ሕክምና አገልግሎት መስጠት የሚችል ተቋም መገንባቱ ህብረተሰቡ አገልግሎት ፍለጋ ርቆ ከመሄድና ከወጪ እንደሚታደገው አመልክተዋል፡፡ መንግስትም የአካባቢውን ህዝብ የረጅም ጊዜ ጥያቄ ሰምቶ በመመለሱ ደስተኛ መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ የጊንጪ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ መሪጊቱ በቀለ በአካባቢያቸው ሆስፒታል ባለመኖሩ ከጤና ጣቢያ ወደ ሆስፒታል ሪፈር ሲጻፍላቸው ወደ አምቦ ከተማ ሆስፒታል በመሄድ ህክምና ያገኙ እንደነበር አስታውሰዋል። በእዚህም በተለይ ነፍሰ ጡር እናቶች በወሊድ ወቅት በሪፈር ተልከው አምቦ ከተማ እስኪደርሱ ድረስ እንግልት ይደርስባቸው እንደነበር አስረድተዋል። በአሁኑ ወቅት በአቅራቢያቸው የተገነባው ሆስፒታል ይሀን እንግለታቸውን ያስቀራል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡ የኤጄሬ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ሄዮ በሰጡት አስተያየት "በጤና ጣቢያው የቀዶ ሕክምና መስጫ ሕንጻ መገንባቱ በተለይ ወላድ እናቶችና ሕጻናት በአቅራቢያቸው ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ ለማድረግ ያስችላል" ብለዋል፡፡ በተለይ ወደሌላ ቦታ ሄደው መታከም ለማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በአገልግሎቱ የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ነው የገለጹት። አቶ ፍቃዱ እንዳሉት ቀደም ሲል ቀዶ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ህሙማን ሲመጡ ወደ አዲስ አበባ እንደሚላኩና አቅም የሌላቸው ከሆነም ህክምና ሳያገኙ በቤታቸው የሚሞቱበት አጋጣሚ ነበር። "በጤና ጣቢያው የቀዶ ሕክምና ሕንጻ መገንባት ይህን ችግር በመፍታት በኩል ጠቀሜታው የጎላ ነው" ብለዋል። በምዕራብ ሸዋ ዞን በአሁኑ ወቅት ስምንት ሆስፒታሎች፣ 91 ጤና ጣቢያዎችና 514 ጤና ኬላዎች ለህብረተሰቡ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።