የፕሬዚዳንት ኢሳያስ የጎንደር ጉብኝት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ያጠናክረዋል-ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የፕሬዚዳንት ኢሳያስ የጎንደር ጉብኝት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ያጠናክረዋል-ነዋሪዎች
ጎንደር ጥቅምት 30/2011 የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ታሪካዊቷን የጎንደር ከተማ ጉብኝት የኢትየጵያና ኤርትራን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንደሚያጠናክረው የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ የከተማ ነዋሪዎች የፕሬዘዳንቱን ጉብኝት ምክንያት በማድረግ ከአጼ ቴዎድሮስ አየር ማረፊያ ጀምሮ አቀባበል አድርጓላቸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድና የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ለፕሬዚዳንት ኢሳያስና ለሶማሊያው ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ታሪካዊና የሁለቱን አገሮች ህዝቦች ዳግም ለማገናኘት ፈር ቀዳጅ በመሆኑ ከልብ አስደስቶኛል ያሉት አቶ አስረስ መሐመድ ናቸው፡፡ ጎንደር የበርካታ ኤርትራውያን መኖሪያ የነበረች፤ ክፉና ደጉንም ጊዜ አብረን ያሳላፍን ወንድማማች ህዝቦች በመሆናችን የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ግንኙነቱን ዳግም ያጠናክረዋል ብለዋል፡፡ ''ጎንደርና አሥመራ ባለፉት ዘመናት ከፍተኛ የንግድና የኢኮኖሚ ትስስር የነበራቸው ታሪካዊ ከተሞች ነበሩ'' ያሉት ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ ሐጂ ማሩፍ ኑርሁሴን ናቸው፡፡ የፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጉብኝት በሁለቱ አገሮች መካከል ተፈጥሮ የቆየውን የሻከረ ግንኙነት ወደ አዲስ የወንድማማችነት ምዕራፍ ያሸጋግራል ብለዋል፡፡ ሁለቱ ከተሞች ቀድሞ የነበራቸው የንግድ ግንኙነት ዳግም አንሰራርቶ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ እውን እንዲሆን የከተማው የንግዱ ማህበረሰብ ፍላጎት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ወይዘሮ በላይነሽ ገብሬ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ታሪካዊቷን ከተማ ለመጎብኘት በመምጣታቸው ህዝቡ አክብሮት መስጠቱን አመላካች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ኤርትራና ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ በጦርነት ውስጥ ቢያልፉም የሁለቱ ህዝቦች ፍቅር አልደበዘዘም ያሉት አስተያየት ሰጪዋ፣በጦርነቱ ወቅትም ቢሆን የከተማው ህዝብ የኤርትራ ወንድምና እህቶቹን አልቅሶ በመሸኘት ፍቅሩን መግለጹን አስታውሰዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ለከተማዋ የህዝብ ተወካዮች በጎሃ ሆቴል ባደረጉት ንግግር ''ጎንደሬም ሆነ ኢትዮጵያዊ አጼ ፋሲል በሰሩት ድንቅ የጥበብ ሥራ የማይኮራ የለም'' ብለዋል፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ለንግሥት ቪክቶሪያ በጻፉት ደብዳቤያቸው ከኢትዮጵያ አልፈው አፍሪካን አንድ እናድርጋት እንዳሉት መጪው ጊዜ የሰላምና የአንድነት እንዲሆን ምኞቴ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡ የጎንደር ከተማ አስተዳደርም ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ በተዘጋጀው የምሳ ግብዣ ላይ የአጼ ቴዎድሮስን ምስል የያዘ ፎቶ በስጦታ አበርክቷል፡፡ ፕሬዘዳንት ኢሳያስ የጎንደር ዩኒቨርሲቲንና የልማት ተቋማትን ጎብኝተዋል፡፡