በአክሱም ከተማ በአምስት ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ አረንጓዴ ልማት ማዕከላት አገልግሎት ጀመሩ

69
አክሱም ጥቅምት 30/2011 በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ በአምስት ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ የወጣቶች የአረንጓዴ ልማት ማዕከላት አገልግሎት መስጠት ጀመሩ። ማዕከላቱ ወጣቶችን ከአልባሌ ስፍራ እንዲርቁ ያደርጋቸዋል፡፡ በአክሱም ማዘጋጃ ቤት የጽዳትና ውበት አስተባባሪ አቶ ጽዮን በርሀ ለኢዜአ እንደተናገሩት አስተዳደሩ በመደበው በጀት የተገነቡት ማዕከላት ሥራ ጀምረዋል። በዚህም 23ሺህ ካሬሜትር ስፋት ያለው የአረንጓዴ ልማት ሥፍራዎችን ያካተቱት ማዕከላት ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ሥፍራዎቹ በአበባ ፣በዛፎችና በሣር  ለወጣቶች መዝናኛና ለማረፊያ አገልግሎት አመቺነት እንዳላቸው አመልክተዋል፡፡ ከተማዋ የቱሪስት መዳረሻ በመሆኗ ለአረንጓዴ ልማት ትኩረት ሰጥታለች ያሉት አስተባባሪው፣በተያዘው ዓመት አንድ ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት በአረንጓዴ ለማልማት አራት ሚሊዮን ብር መመደቡን ገልጸዋል። የሓወልት ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ኢየሩስ ጌታሁን በማዕከሉ ትኩስ መጠጥ አዘጋጅታ በመሸጥ በቀን እስከ 200 ብር ገቢ እያገኘች መሆኗን ተናግራለች፡፡ በከተማው የሓየሎም ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሚኪኤለ ገብረመድኅን እንዳሉት አሁን በአረንጓዴ ፓርክ የለማው ሥፍራ ከዚህ በፊት ለዓይን የማይማርክና የቆሻሻ መድፊያ እንደነበር አስታውሰው፣አሁን አዛውንቶችና ወጣቶች መዝናኛ ከመሆኑም በላይ፤ በተጨማሪ ለወጣቶች የገቢ ምንጭ በመሆኑ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል፡፡ በአክሱም ዩኒቨርስቲ የኮምፒተር ሳይንስ አንደኛ ዓመት ተማሪ እስራኤል ጌታቸው ሥፍራዎቹ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችና ወጣቶች በትርፍ  ሰዓታቸው አልባሌ ቦታዎች እንዳይሄዱና ለሱስ እንዳይጋለጡ ያደርጋል  ብሏል።                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም