ቀጥታ፡

የኤርትራና የሶማሊያ ፕሬዚዳንቶች ጎንደር ገቡ

አዲሰ አበባ  ጥቅምት 30/2011 የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂና የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሙሐመድ አብዱላሂ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ ግብዣ ዛሬ አማራ ክልል ጎንደር ከተማ ገብተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የሱማሌ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ ኡመርና  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጎንደር አፄ ቴዎድሮስ አውሮፕላን ጣቢያ በመገኘት ለፕሬዚዳንቶቹ አቀባበል አድርገዋል። የፕሬዚዳንቶቹ የኢትዮጵያ ጉብኝት በአፍሪካ ቀንድ ሰላም ላይ አዎንታዊ ተፅእኖ እየፈጠረ የሚገኘው የለውጥ ሂደትና የምጣኔ ኃብታዊ ትብብርን ለማመቻቸት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚያካሂዱት እንቅስቃሴ አካል እንደሆነም ተመልክቷል። ባለፈው ወር በኤርትራ አስመራ የተካሄደው የሶስቱ አገራት የጋራ ምክክር ተከታይ የሆነው ይህ ጉብኝት በአገራቱ መካከል የተጀመረውን ውይይት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ያለመ ነው፡፡ መሪዎቹ በባህር ዳር ከተማ በመሰብሰብ በአህጉራዊ፣ ቀጠናዊና አለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረክ ይመወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል። መሪዎቹ በተለይም በቀጠናው መረጋጋትና ሰላም መፍጠር፣ ምጣኔ  ትስስር ማጠናከርና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይም ይመክራሉ ተብሏል። ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያና ኤርትራ ሁሉን አቀፍ የሶስትዮሽ ስምምነት አስመራ ላይ ነሀሴ  30 ቀን 2010 ዓ.ም  ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። መሪዎቹ በጎንደርና ባህር ዳር የሚገኙ የልማት እንቅስቃሴዎችን እንደሚጎበኙም ይጠበቃል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ትናንት ምሽት በጎንደር ከተማ ከአካባቢው ሽማግሌዎች፣ ከሐይማኖት አባቶችና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በሰላምና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም