ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን ተመሰረተ

አዲ አበባ ግንቦት 15/2010 የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን ዛሬ በአዲስ አበባ በተካሄደ ጠቅላላ ጉባኤ በይፋ ተመሰረተ። 'ብዙ ስራ ለብዙ ዜጎች' በሚል መሪ ሃሳብ የተመሰረተው ኮንፌዴሬሽኑ በአሰሪ፣ ሰራተኛና መንግስት የሶስትዮሽ ግንኙነትን በማመቻቸት የተረጋጋ ኢንዱስትሪ ለመፍጠር የጎላ ሚና ይኖረዋል ተብሏል። ኮንፌዴሬሽኑን ለመመስረት ባለፉት 10 ወራት ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን የኮንፈዴሬሽን የአደራጅ ምክር ቤቱ ሰብሳቢና የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው ኃይሌ ተናገረዋል። በዛሬው ዕለትም የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሰራተኛች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ተወካዮች፣ የግሉ ዘርፍ አደረጃጅቶችና የመስራች አባላት በተገኙበት በተካሄደ የአደራጅ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤ ነው ኮንፌዴሬሽኑ በይፋ የተመሰረተው። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የዓለምን ትኩረት የሳበ ነው ያሉት አቶ ጌታቸው፤ የኢንዱስትሪ ሰላም ማስፈን የጋራ ተጠቃሚነትን ለማዳበርና አሰሪዎች ለአገራዊ ዕድገቱ ያላቸውን ድርሻ ይበልጥ እንዲያጎብቱ ያስችላል ብለዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ የተመሰረተው ኮንፌዴሬሽኑ ሁሉንም ወገን የያዘና የሁሉን ድምጽ በማካተት የአሰሪዎች ፌዴሬሽኖችን የመደራደር አቅም ለማጎልበት፣ መብታቸውን ለማስከበርና ግዴታቸውንም በዕውቀት ላይ ተመስርተው እንዲወጡ ያግዛል ነው ያሉት። የሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጭ አሰሪዎች፣ የኢትዮጵያ ከተሞች ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት አሰሪዎች፣ ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አሰሪዎች፣ የአማራ ክልል አሰሪዎች እና የአዲስ አበባ ከተማ አሰሪዎች ፌዴሬሽኖች መስራች አባላት ናቸው። በኢትዮጵያ ስድስት የአሰሪዎች ፌዴሬሽኖች መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፤ ኮንፌዴሬሽኑን ለመመስረት በነበረው ሂደት 'ከኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን' በስተቀር ቀሪዎቹ አንድ ኮንፌዴሬሽን ለመመስረት ተስማምተው መወሰናቸውን አብራርተዋል። 'ድህነትን ማስወገድ የሚቻለው የስራ ዕድል የፈጠረ ኢንቨስትመን ሲስፋፋ ነው' ያሉት የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ፤ አሰሪና ሰራተኛ መካከል የማህበራዊ ምክክር ለመፍጠር መደራጀት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል። የተመሰረተው ኮንፌዴሬሽን ለተረጋጋ የኢንዱስትሪ፣ ለምርታማነት፣ ለተወዳዳሪነት፣ ለስራ ዕድል ፈጠራ፣ ማኅበራዊ ምክክርና የአሰሪ፣ ሰራተኛና በመንግስት መካከል የሰመረ የሶስትዮሽ ግንኙነት እንዲኖር ያስችላል ብለዋል። በየትኛውም የስራ መስክ አለመግባባት እንደሚፈጠር የገለጹት አቶ ካሳሁን፤ ወደፊት የሰራተኛና የአሰሪ ኮንፌዴሬሽኖች በጋራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። የሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ሒሩት ወልደማርያም በተወካያቸው ባስተላለፉት መልክት መደራጀት ህገ-መንግስታዊ መብት መሆኑን ጠቅሰው፤ የአሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን መመስረቱም መንግስት ላወጣቸው ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ተግባራዊነት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል። ኮንፌዴሬሽኑ የአሰሪዎችን መብትና ጥቅም ከማስከበር ባለፈ በሚፈጠሩ አለመግባባቶች መፍትሔ ማበጀት፣ የሕግ ማዕቀፎችን ለማውጣት፣ በአካባቢ ጥበቃና ሌሎች ማኅበራዊ ኃላፊነቶችን ለመወጣት የላቀ ሚና እንደሚኖረው አብራርተዋል። እነዚህን አገራዊ ፋይዳዎች ታሳቢ በማድረግም መንግስት የኮንፌዴሬሽኑን መቋቋም እንደሚደግፍና ወደፊትም ለኮንፌዴሬሽኑ መጠናከር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። የዓለም አቀፍ የስራ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ደረጃ ዓለሙ የኮንፌዴሬሽኑ መመስረት ለድርጅቱ ተጨማሪ አቅም እንደሆነ ገልጸው የድርጅቱን አጋርነት አረጋግጠዋል። ኮንፌዴሬሽኑ በኢንዱስትሪ፣ በግንባታ፣ በጤና፣ በትራንስፖርት፣ በግብርና፣ በጥበቃና ሰው ኃይል አቅርቦትና ሌሎች ዘርፎች የተደራጁ ማኅበራትን አቅም በመገንባት ወደ ፌዴሬሽንነት ማሳደግን ቀዳሚ ተግባሩ እንደሚያደርግ ገልጿል። ከምስረታው በኋላ የጠቅላላ ጉባኤው ውይይት የቀጠለ ሲሆን ከሰዓት በኋላም የኮንፌዴሬሽኑን የዳይሬክተሮች ቦርድ አመራር አባላትና የፕሬዝዳንት ምርጫ ያካሂዳል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም