ቀጥታ፡

የኤሌክትሪክ ታሪፍ ከማስተካከል ጎን ለጎን አገልግሎቱንም በጥራት ለማሳደግ መሰራት አለበት

አዲስ አበባ ጥቅምት 29/2011 የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከታሪፍ ማስተካከያው ባሻገር የአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ማሻሻያ ማድረግና ጥራቱን ማሳደግ  እንደሚያስፈልግ ተገለጸ። የተደረገው የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማስተካከያ የወቅቱን አገራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ቢሆንም የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ጠንካራ ተግባር እንደሚጠበቅበት የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎችና አምራች ማህበራት አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከመካከለኛና ከከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች፣ ከአምራች ማህበራትና ከመንግስት ተቋማት ተወካዮች ጋር በኤሌክትሪክ አገልግሎት ታሪፍ ማስተካከያና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ ዛሬ አገር አቀፍ የምክክር መድረክ አካሂዷል። አሁን በስራ ላይ ያለው የኤሌክትሪክ ታሪፍ ምንም አይነት ማስተካከያ ሳይደረግበት ላለፉት 12 ዓመታት ሲሰራበት ቆይቷል። በዚህም ከደንበኞች እየተሰበሰበ ያለው የአገልግሎት ክፍያ አነስተኛ በመሆኑ የአገሪቱ ኢኮኖሚ፣ ኢንዱስትሪዎች፣ የንግድ ተቋማትና የከተሞች መኖሪያ ቤቶች መስፋፋት አንጻር የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ተመጣጣኝ አልሆነም። በዚህም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከመጪው ታህሳስ 2011 ዓ.ም ጀምሮ የታሪፍ ማስተካከያ እንደሚያደርግ መግለጹ ይታወቃል። ይሁንና ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ታሪፍ ማስተካከያው ባሻገር ህብረተሰቡ በብዛት የሚያነሳቸውን የሃይል መቆራረጥና የአገልግሎት ጥራት ላይ ጠንካራ ስራ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል። ከስጋ ላኪዎች ማህበር የመጡት አቶ አበባው መኮንን እንዳሉት፤ የታሪፍ ማስተካከያው አገሪቱ አሁን ካለባት የውጭ ምንዛሬ፣ የዋጋ ግሽበትና ሌሎችም ምክንያቶች ጋር በተያያዘ ተገቢነት አለው። ይሁንና ከታሪፍ ማስተካከያው ባሻገር የአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የተጠናከረ ስራ መሰራት እንዳለበት ገልጸዋል። ከኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር የመጡት አቶ ጸጋ አበበ በበኩላቸው በአገልግሎቱ ላይ በተለይ ከጥራት ጉድለት ጋር በተያያዘ በርካታ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች የሚነሱ በመሆናቸው መፈታት እንዳለባቸው ተናግረዋል። ስለተደረገው የታሪፍ ማስተካከያና አስፈላጊነት በተለይ በውጭ ድርጅቶች፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በፋብሪካዎች ላይ ለተሰማሩ ባለሃብቶች ግንዛቤ መፈጠር አለበት ያሉት ደግሞ ከኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የመጡት አቶ ዳግም ተረፈ ናቸው። የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኤሌክትሪክ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍሬህይወት ወልደሃና እንደገለጹት፤ ጥራቱን የጠበቀ፣ አስተማማኝ እና ዘላቂነት ያለው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለተገልጋዮች ለማቅረብ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም እየተሰራ ይገኛል። ይሁንና እያደገ ከመጣው የህብረተሰቡ የሃይል ፍላጎት፣ የአገሪቱ የቆዳ ሽፋንና የከተሞች ብዛትና ስፋት አንጻር አጥጋቢ አገልግሎት መስጠት አልተቻለም። የግብአት አቅርቦት እጥረት፣ የማከፋፈያ መስመሮች እርጅናና በዚህም የሃይል ጭነት የሚበዛባቸውና የአገልግሎት መቆራረጥ የሚያስከትሉ መሆናቸው እንዲሁም የኔትዎርክ ማኔጅመንቱ ዘመናዊ አለመሆን ለከፍተኛ የሃይል ብክነትና ለደንበኞች ጥያቄ ፈጣን ምላሽ መስጠትም እንዲሁ። በዚህም አሁን ላይ ያለው የኤሌክትሪክ ታሪፍ አገልግሎቱን ለማቅረብም ሆነ የሚወጣውን ወጪ ለመመለስ የሚያስችል ባለመሆኑ የታሪፍ ማስተካከያ ማድረግ አስፈላጊ ሆኗል ብለዋል። በመሆኑም ችግሮቹን ለመፍታት ያረጁና የተጨናነቁ ማከፋፈያ መስመሮችን ማሻሻል፣ አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ የመደገፍ፣ የማዘመንና የሃይል ብክነቱ እንዲቀንስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ከልማት አጋሮች ጋር የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን የማስፋፋት፣ መልሶ የመገንባትና የማሻሻል ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም አክለዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም