ቀጥታ፡

የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት የሚደረግልን ድጋፍና ክትትል አናሳ ነው አሉ

አዲስ አበባ ግንቦት 15/2010 የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት የሚደረግላቸው ክትትልና ድጋፍ አናሳ መሆኑን ተናገሩ። የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ ከተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ጋር በጋራ በመሆን የኤጀንሲውን የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ገምግመዋል። ከክልልና ከከተማ የመጡ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት በዚህ ወቅት እንደገለጹት የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ለህብረተሰቡ እየሰጡ ያሉት ጠቀሜታ ከፍተኛ ቢሆንም የሚደረግላቸው ድጋፍና ክትትል ግን አናሳ ነው። በሐዋሳ አጂጃ የህጻናት መርጃ ማዕከል የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ገነነ ካዊሶ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራትን በአካል በመገኘትና ችግሮቻቸውን በማየት ረገድ የሚደረገው ድጋፍና ክትትል አናሳ መሆኑንና ክፍተቶችም በመኖራቸው በቂ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል ብለዋል። የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ቃልኪዳን ሽመልስ በበኩላቸው እንደነዚህ ያሉ ድርጅቶች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በማጠናከር አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ እገዛ መደረግ አለበት ይላሉ። የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ ከተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር ተቀራርቦ በመስራት ረገድ ክፍተቶች አሉበት ያሉት ደግሞ የኦ አይ ሲ ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ እያሱ ኃይሉ ናቸው። በመሆኑም ኤጀንሲው ከድርጅቶች ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር፣ ችግሮችን በመለየትና በመፍታት የተጠናከረ ስራ መስራት ይገባዋል ነው ያሉት። ኤጀንሲው በበኩሉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ተደራጅተው በአገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገትና ልማት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ለማድረግ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጿል። የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፋንታዬ ገዛኽኝ እንዳሉት፤ ኤጀንሲው ካለው የሰው ኃይልና በሌሎችም ምክንያቶች የሚፈለገውን ያህል የክትትልና የድጋፍ ስራዎችን እየሰራ አይደለም። በመሆኑን በቀጣይ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት የድጋፍና ክትትል ስራውን ለማጠናከርና ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም