ጠዋት! ጠዋት!

84
ሚስባህ አወል/ኢዜአ/ የጥቅምት ወር እየተገባደደ ነው፡፡  በፀደዩ ወራት  ኩልል ብላ በጠራው ሰማይ ላይ በጠዋቱ የፈነጠቀችዋ የማለዳ ጮራ ደማቅ ፈገግታዋን ቸራለች፡፡ ፈገግታዋ ቀስ በቀስ እየከረረ መጥቶ ረፋድ ላይ በከባድ ሙቀቷ አናት መሰንጠቅ ትጀምራለች፡፡ ለተለያየ ጉዳይ በመዲናዋ ውር ውር የሚሉ መንገደኞችም በተለይ ሴቶች ክረምት ከዝናብ የሚጠለሉበትን ጃን ጥላ እየከረረ የመጣውን የጸሀይ ሙቀት ለመከላከል ይጠቀሙበታል፡፡ ሙቀቱን ለመከላከል በየቤቱ ለመደበቅ የሚሯሯጡትና በየዛፉ ጥላ ስር ተጠልለው ለማሳለፍ የሚሞክሩትም ያን ያህል ብዙ ናቸው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ  የመጣው የቤት ኪራይ ዋጋ ከመሃል ከተማ ርቄ በአዲስ አበባ አንደኛው ጫፍ እንድኖር አስገድዶኛል፡፡ ከስራ ገበታዬ በጣሙን በመራቄ በሰዓቱ ስራ ቦታ ለመድረስ ጎህ ሳይቀድ ጉዞ መጀመር ይጠበቅብኛል፡፡ ዛሬም እንደወትሮው ወደ ስራ ገበታዬ ጉዞ የጀመርኩት በጠዋቱ ነው፡፡ እንደነገሩ ጥርብ ድንጋይ  የተነጠፈለት መንገድ እንደ ልብ ለመንቀሳቀስ ቢያስችግርም እየተጣደፍኩ ወደ አስፓልት ወጣሁ፡፡ ትራንስፖርት ፈላጊው ሰልፍ እንደ አባይ ወንዝ ተጠማዝዞ መጨረሻውን ለማየት ይናፍቃል፡፡  እኔም ታክሲ ፍለጋ ጊዜ ማባከን አልፈለኩም፡፡ በቀጥታ ሳንሱሲ አካባቢ ወዳለው የብዙኃን ትራንስፖርት መሳፈሪያ ጣቢያ አመራሁ፡፡ ቶሎ ለመድረስ ካለኝ ጉጉት የተነሳ ሁለት ሶስት ፌርማታዎችን እየዘለለ የሚጓዘውን ሸገር የብዙኃን ትራንስፖርት አውቶብስን ምርጫዬ አደረግኩ፡፡ ራስደስታ ሆስፒታል አካባቢ እስከምደርስ በሰፊው መስዋዕት የመንገዳችንን ግራና ቀኝ ጠርዝ እያማታርኩ በርካታ ርእሰ ጉዳዮችን አወጣሁ፤ አወረድኩ፡፡ ከሁሉም ቀልቤን የሳበው ግን በየቦታው ያለው የታክሲ ሰልፍ ነው፡፡ በየመንገዶቹ የቀኝ ጠርዝ በረዥሙ የተሰለፉ ትራንስፖርት ፈላጊዎች ወታደራዊ ትዕዛዝ የተሰጣቸው ይመስል አንገታቸውን ወደ ግራ አዙረው አልፎ አልፎ ብቅ የሚሉትን ታክሲዎች በጉጉት ይጠባበቃሉ፡፡ ሰልፈኞቹ በጉጉት የሚጠብቋቸው ታክሲዎች ግን ጠዋት ጠዋት ስራ የቀየሩ ይመስላል፡፡ ውር ውር የሚሉት ታክሲዎች ተማሪዎችን እጭቅ  አድርገው ይከንፋሉ፡፡ በአንድ ታክሲ ውስጥ መሳፈር ያለበት የህዝብ ብዛት ተማሪዎች ላይ የሚሰራ አይመስልም፡፡ የተማሪ ትርፍ የለውም እንዴ? የሚል ሀሳብ እያውጠነጠንኩ ጉዞዬን ቀጥያለሁ፡፡ በዚህ ጊዜ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት እኔ የተሳፈርኩበትን ጨምሮ ሌሎች የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሸከርካሪዎች ናቸው፡፡ እንደ እኔ በመስኮት አሻግረው የትራንስፖርት ፈላጊውን ሰልፍ የተመለከቱ አንድ አዛውንትም ጉዳዩ ቢያሳሰባቸው ድምጻቸውን ከፍ አድርገው “ወይ ጉድ! በትራንስፖርት አጦት ይኼ ሁሉ ሰው እንዲህ ይንገላታ?” የሚል ጥያቄ ሰነዘሩ፡፡ ማንን እንደጠየቁ ባይገባኝም ዞር ብዬ አየኋቸው፤ ጉዳዩ የኔ ብቻ አለመሆኑንም ተረዳሁ፡፡ እንዲያው ግን የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ችግር የሚቃለለው መቼና እንዴት ይሆን? ከዓመታት በፊት በአንበሳ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ደርጅትና በተወሰኑ ታክሲዎች ይስተናገድ የነበረው የመዲናዋ ህዝብ ቁጥሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ በአቅርቦቱና ፍላጎቱ መካከል ሰፊ ክፍተት ተፈጥሯል፡፡ አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ የቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎትን ጨምሮ የተለያዩ የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎቶች ስራ ቢጀምሩም ችግሩን ማቃለል አልተቻለም፡፡ ከራሴ ጋር በሀሳብ እየተሟገትኩ ራስ ደስታ ሆስፒታል ስደርስ ወረድኩ፡፡ እዚህም ሌላ ቀልቤን ቆንጠጥ የሚያደርግ ጉዳይ ገጠመኝ፡፡ በሁለቱም አቅጣጫ ያለው መንገድ በተሸከርካሪ ተጨናንቋል፡፡ ብዙም እንቅስቃሴ የለም፡፡ ተሸከርካሪዎቹ ከእርምጃ ባነሰ ፍጥነት ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡ ኧረ እንዲያውም ጉዳይ ያለበት ሰው ተሸከርካሪ ከሚጠቀም ይልቅ በፍጥነት ቢራመድ  ካሰበው ቦታ በፍጥነት መድረስ ይችላል፡፡ አስፓልት ለማቋረጥ ቆሞ መጠበቅ የማይታሰብ ነው፡፡ የተሸከርካሪዎቹ ፍጥነት በመንገዱ መጨናነቅ ስለተገታ አብዛኛው ሰው ተሸከርካሪዎቹ ቆመው እስከሚያሳልፉት አይጠብቅም፡፡ በተሸከርካሪዎቹ መሃል እየተሸሎከሎከ ይሻገራል፡፡ እኔም እንዲሁ ነው የተሻገርኩት፡፡ የአዲስ አበባን የትራንስፖርት እጥረት ለመቅረፍ የተሸከርካሪዎችን ቁጥር መጨመር ብቻውን የተሟላ መፍትሔ ሊያመጣ እንደማይችል ተገነዘብኩ፡፡ እኔ እንኳን ከመነሻዬ እስከመዳረሻየ ያለው እርቀት ከ10 ኪሎ ሜትር ያነሰ ቢሆንም የፈጀው ጊዜ ከአንድ ሰዓት በላይ መሆኑን ስገነዘብ ችግሩ የተሸከርካሪዎች እጥረት ብቻውን የወለደው አለመሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ የመንገድ መሰረተ ልማቱ የወቅቱን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ አስገብቶ ቢሆን ኖሮ የትራፊክ መጨናነቁን በመቀነስና ያሉትን ተሸከርካሪዎች ምልልስ በመጨመር ችግሩን ማቃለል ይቻል ነበር፡፡ የአዲስ አበባን የትራንስፖርት እጥረት ለመቅረፍ ከተፈለገ ሁለቱንም አብሮ ማስኬድ ካልሆነም የመንገድ መሰረተ ልማቱን በማስፋፋት ችግሩን ለማቃለል መሞከሩ አዋጪ ሳይሆን አይቀርም፡፡ መንገዶቻችን ወርድና ርዝመታቸው የረባ ማሻሻያ ሳይደረግባቸው በየዓመቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ተሸከርካሪዎች ወደ መዲናዋ እየገቡ መሆኑን መስማት ደግሞ ችግሩ እየተባባሳ ሊሄድ እንደሚችል ለመገመት ያስችላል፡፡ የመንገዱ መጨናነቅ ፍጥነትን ከመግታቱም ባሻገር በየእለቱ ለሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎችም ተጠቃሽ ምክንያት ነው፡፡ ችግሩ ሳይባባስና ሌላ ችግር ይዞ ሳይመጣ አዳዲስና አማራጭ የመንገድ ማስፋፊያ ስራዎችን ከወዲሁ አቅዶ መስራት ብልህነትም አዋቂነትም ነው፡፡ ከመነሻዬ እስከ መዳረሻዬ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን እያወጣሁና እያወረድኩ ከቢሮዬ በር ደርሼ ራሴን ለፍተሻ ሳዘጋጅ ወደ ራሴ ተመለስኩ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም