ቀጥታ፡

አየር መንገዱ በ100 አውሮፕላኖች አገልግሎት በመስጠት በአፍሪካ ቀዳሚ ሊሆን ነው

አዲስ አበባ ግንቦት 15/2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ100 አውሮፕላኖች አገልግሎት በመስጠት በአፍሪካ አቪዬሽን ታሪክ የመጀመሪያው የአየር መንገድ ሊሆን ነው። የፊታችን ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም በግዢ ያዘዘውን ቦይንግ 787 900 ሲረከብ በአፍሪካ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 100 አውሮፕላን ያለው አየር መንገድ እንደሚሆን አየር መንገዱ ለኢዜአ በላከው የፕሬስ መግለጫ አስታውቋል። ታሪካዊው ሁነት አየር መንገዱ በሁሉም መስኮች በአፍሪካ የአቪዬሽን አገልግሎት መሪነቱን የሚያሳይና በኢቪዬሽን ቴክኖሎጂ ግንባር ቀደም ሚናውን የሚያመላክት እንደሆነ ተገልጿል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም አየር መንገዱ 100 አውሮፕላኖችን መጠቀም ላይ ለመድረስ መቃረቡ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያኮራ ነው ብለዋል። በ100 አውሮፕላኖች አገልግሎት የመስጠት አቅም ላይ መደረሱ አየር መንገዱ በአፍሪካ አቪዬሽን ያለውን ታሪክ የሚያስቀጥልና ፈጣን፣ትርፋማና ዘላቂነት ባለው መልኩ በስኬት እየተገበረ ያለው ራዕይ 2025 ስራን የሚያሳይ ነው ሲሉ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ከአምስት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ 100 ዘመናዊ አውሮፕላኖችን መጠቀም መቻሏ የአገሪቱ የአቪዬሽን ዘርፍ የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ የሚያመላክት እንደሆነ አየር መንገዱ ገልጿል። አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት ዘመናዊ የሆኑትን ቦይንግ 787 እና ኤርባስ 350 አውሮፕላኖችን በመግዛት ለተሳፋሪዎች ምቹ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝና ደንበኞቹን አፍሪካን ከሌላው ዓለም ጋር የማገናኘት ተግባር በስፋት እያከናወነ እንደሆነ አስታውቋል። የ100 አውሮፕላን አገልግሎት የመስጠት የ2025 ራዕይ ቀድሞ በመሳካቱ ማሻሻያ በማድረግ ተጨማሪ አውሮፕላኖችን በመግዛት በአፍሪካ ያለውን የጉዞ ፍላጎት ለማሟላትና የኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝምና የንግድ ፍሰቱን በማመቻቸት ለአህጉሪቱ ኢኮኖሚያዊ ልማትና ትስስር እንደሚሰራም ተጠቅሷል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1962 በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የጀት ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የጀመረ አየር መንገድ ነው። በተጨማሪም አየር መንገዱ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2012 ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን እንዲሁም በ2016 ኤር ባስ ኤ350 ደብሊው ኤክስ ቢ አውሮፕላንን በመግዛትና በመጠቀም በአፍሪካ የመጀመሪያው አየር መንገድ እንደሆነም ይታወቃል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአምስት አህጉራት ከ110 በላይ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች አሉት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም