ቀጥታ፡

አረጋዊያን ለዘላቂ ሰላም መስፈን የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ ጥቅምት 28/2011 በአገሪቷ የሚስተዋሉ የጥፋት ድርጊቶች እንዲታረሙና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን አረጋዊያን የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ። "ቀደምት የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾችን በመዘከር የኢትዮጵያ አረጋዊያንን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እናረጋግጥ" በሚል መሪ ሃሳብ በዓለም ለ28ኛ በአትዮጵያ ለ27ኛ ጊዜ የተከበረው የአረጋዊያን ቀን የማጠቃለያ ሥነ ስርዓት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬም በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚከሰቱ የጥፋት ድርጊቶችን ለማረም አረጋዊያን እውቀትና ጥበባቸውን ተጠቅመው ለዘላቂ ሰላም መስፈን እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል። አረጋዊያን የማስታረቅና መፍትሄ የማመንጨት የዳበረ ልምዳቸውን በመጠቀም ሰላም የማስፈን ተግባራቸውን እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል። በሌላ በኩል መንግስት የአገርና የትውልድ ባለውለታ የሆኑት አረጋዊያን በእርጅና ዘመናቸው የሚደርሱባቸውን ችግሮች ለማቃለል  ቀጣይነት ያላቸውን ተግባራት በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። የአስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጡ አዋጆች ሁሉም የመንግስት አስፈጻሚ አካላት የአረጋዊያንን ጉዳይ በማካተት እንዲሰሩ ግልጽ አቅጣጫ መቀመጡ 'ለጉዳዩ የተሰጠውን ትኩረት ያሳያል' ብለዋል ሚኒስትሯ። የአረጋዊያን የልማት ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲጎለብት በማድረግ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸው እንዲቃለሉ ከፌዴራል እስከ ክልሎች መዋቅር ተዘርግቶ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። የአትዮጵያ አረጋዊያን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አባሙዳ አበበ ኃይሉ በበኩላቸው ማህበሩ የአረጋዊያንን መብትና ጥቅም ለማስከበር እየሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት። በኢትዮጵያ ከሚገኙ ከስድስት ሚሊዮን በላይ አረጋዊያን መካከል 'አብዛኞቹ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች አሉባቸው' ያሉት ፕሬዚዳንቱ መንግስት ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም