ጥቅምት 30 ይካሄዳል የተባለው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዘመ - ኢዜአ አማርኛ
ጥቅምት 30 ይካሄዳል የተባለው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዘመ
አዲስ አበባ ጥቅምት 28/2011 በተያዘው ወር መጨረሻ እንደሚካሄድ ተገልጾ የነበረው የ40/60 እና 20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ሥነ-ስርዓት ላልተወሰነ ጊዜ ተራዘመ። የአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ቢሮ ከ42 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለማስተላለፍ ጥቅምት 30 ቀን 2011 ዓ.ም የዕጣ አወጣጥ ስነ-ስርዓት እንደሚካሄድ ገልጾ ነበር። ቢሮው ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የዕጣ ማውጣቱ ስራ 'ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል' ብሏል። ለዚህ ምክንያት ያለው ደግሞ ቀደም ሲል ዕጣ ይወጣበት የነበረው ሶፍትዌር ሲስተም በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ /ኢንሳ/ ስር የነበረ መሆኑንና ይህም የህጋዊነትና የፍትሃዊነት ጥያቄ ማስነሳቱን ነው። ሶፍትዌር ሲስተሙን መፈተሽና የተጠያቂነት ሥርዓት መዘርጋት በማስፈለጉም ቢሮው በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሰረት ሶፍትዌሩን የመገንባትና የማስተዳደሩን ስራ ተረክቦ እየሰራ መሆኑ ተነግሯል። ቀደም ሲል የተካሄደው የዕጣ አወጣጥ ችግር ነበረበት ወይ? ተብሎ ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የቢሮው ምክትል ኃላፊ ኢንጂነር ዘሪሁን አምደማሪያም የተረጋገጠ ነገር እንደሌለ፣ የኦዲት ሥራ እየተሰራ መሆኑንና ግኝቱም ይፋ እንደሚደረግ ገልፀዋል። የ40/60 ቤቶችን ተረክቦ የማስተላለፍ ኃላፊነት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደነበር ያወሱት ምክትል ኃላፊው ይህም አሰራር ተገቢ ባለመሆኑ ውሉ ተቋርጦ ቤቶቹን የሚገነባው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቢሮ 'እንዲያስተላልፈው ተደርጓል' ብለዋል። ለዕጣው መዘግየት ተብለው የተጠቀሱት ችግሮች ተፈተው በቅርቡ ቤቶቹ ለዕድለኞች እንደሚተላለፉም ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ከ94 ሺህ በላይ ቤቶች በግንባታ ሂደት ላይ ሲገኙ 21 ሺህ 720 የመኖሪያና 1 ሺህ 171 የንግድ ቤቶች ግንባታቸው ከ80 በመቶ በላይ ተጠናቋል። ከ38 ሺህ በላይ የ40/60 ቤቶችም በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ ሲሆን ለ17 ሺህ 737 ቤቶች የግንባታ ማጠናቀቂያ ሥራዎች እየተሰሩ በመሆኑ ዕጣ ውስጥ የሚገቡ ናቸው። በአጠቃላይ በ40/60 እና 20/80 ፕሮግራሞች የግንባታ ሂደታቸው የተጠናቀቁ 42 ሺህ 341 ቤቶች ለተጠቃሚዎች ይተላለፋሉ ተብሏል። የህንፃ ውስጥ ቀሪ የማጠናቀቂያ ሥራዎች በአጭር ጊዜ የሚከናወኑ ሲሆን የተወሰኑ ቤቶችም ዕድለኞቹ ከታወቁ በኋላ እንደሚጠናቀቁ ተገልጿል።