ሴቶች የሚያጋጥማቸውን የገንዘብ ችግር ለመፍታት የፖሊሲ ማሻሻያ ለማድረግ የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሴቶች የሚያጋጥማቸውን የገንዘብ ችግር ለመፍታት የፖሊሲ ማሻሻያ ለማድረግ የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ ጥቅምት 28/2011 በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ሴቶች የሚያጋጥማቸውን የገንዘብ ችግር ለመፍታት የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ የሚያስችል ጥናት እያካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አስታወቀ። ለአገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሴቶች ከጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ወጥተው የትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ባለቤት እንዲሆኑ ማስቻል ቁልፍ ተግባር ነው። በተለይም ወጣት ሴቶች የሥራ ፈጣሪነት ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ተፎካካሪ ምርቶችና አገልግሎቶችን ማቅረብ እንደሚችሉ ይታመናል። ይሁንና በአገሪቱ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ብድር ለማግኘትና ሌሎች መሰል ተግባራት ጋር በተያያዘ ያሉት ችግሮች ውስብስብ መሆናቸው ሲገለጽ ይስተዋላል። ምንም እንኳን ወደ ንግድ ሙያ ለመግባትና ለመሰማራት የሚፈልጉና አቅሙ ያላቸው በርካቶች ቢሆኑም ስራ መጀመሪያና ማስኬጃ ገንዘብ የማግኘትና በተለያዩ መስኮች ተሰማርቶ ለመስራት ችግር መኖሩ ደግሞ በዋናነት የሚነሳ ነው። ችግሩን ለመፍታት የፖሊሲ ማሻሻያ እንዲደረግ ጥናት እያካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የንግድና ኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ቢንያም ምስግና ለኢዜአ ተናግረዋል። በቅድሚያ ከሴት ነጋዴዎች ጋር ቀርቦ በመነጋገርና ውይይት በማካሄድ መፈታት የሚገባቸውና መጨመርም ሆነ መቀነስ ያለባቸውን ጉዳዮች በመለየት በቀጣይ የፖሊሲ ማሻሻያ እንዲደረግ ለመንግስት የሚቀርብ መሆኑን ተናግረዋል።