ቀጥታ፡

መንግስት የግጭቶችን ምንጭ በማጥናት መፍትሄ እንዲፈልግ የምስራቅ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች ነዋሪዎች ጠየቁ

አዲስ አበባ ጥቅምት 28/2011 መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችን መነሻ መንስኤ በማጥናት መፍትሄ እንዲፈልግ የምስራቅ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች ነዋሪዎች ጠየቁ። ነዋሪዎቹ ይህን የተናገሩት ዛሬ በድሬድዋ ከተማ በተጀመረው የሰላም ኮንፍረንስ ላይ ነው። በሰላም ኮንፈረንሱ የሚሳተፉት አምስቱ የምስራቅ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች አፋር፣ ሐረሪ፣ ሶማሌ፣ ኦሮሚያ ክልሎችና ድሬዳዋ አስተዳደር ናቸው። በመድረኩ ላይ ለውይይት መነሻ የሚሆን ጽሁፍ “ብዝሃነት፣ መቻቻልና እርቅ ለአገራዊ አንድነት ግንባታ” በሚል  ርዕስ ቀርቧል። በቀረበው ጽሁፍ ላይ ከአምስቱ የምስራቅ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች የተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ ወጣቶችና ሌሎች ተሳታፊዎች ሃሳብ ሰጥተዋል። በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች መነሻቸው ከነዋሪዎች ሳይሆን ሌሎች የሚፈጥሩት ነው የሚለው የሃሳባቸው ማጠንጠኛ ነበር። ''መቻቻል ከሌለ አገር የለም፣ ኢትዮጵያን አንድ ሆነን ተከባብረንና ተቻችለን እንገንባት፣ የኢትዮጵያን ብሄረሰቦች አንድነት የማይፈልጉ ህዝቦቿን ለመነጣጠል የሚያሴሩት በመሆኑ ልንነቃባቸው ይገባል'' የሚሉ ሃሳቦችን አንስተዋል። የተወሰኑ መገናኛ ብዙሃን በዘገባቸው ወገንተኝነት እንደሚስተዋልባቸው በማንሳት መገናኛ ብዙሃን ከአድሏዊ አዘጋገብ የጸዱ ሊሆኑ እንደሚገባም ጠቁመዋል። በህዝቦች መካከል እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶች በህዝቦች ላይ የፖለቲካ ንግድ እየተካሄደ መሆኑን ያነሱት ተሳታፊዎች ድርጊቱ ሊቆም እንደሚገባ ተናግረዋል። በዚህም አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላም ፈላጊ ቢሆንም የተወሰኑ ግለሰቦች የመንግስት ሃላፊዎችን ጨምሮ በሚፈጥሩት ሴራ ሰላማቸው እየተረበሸ መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም ለሚፈጠሩ ግጭቶች የውይይት መድረኮችን ከማዘጋጀት ባለፈ በጥናት ላይ የተመሰረተ መፍትሄ መንግስት ሊያበጅ እንደሚገባ በመጠቆም ለዚህም ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል። መንግስት ህግን በማስከበርና ችግር ፈጣሪዎችን ለህግ በማቅረብ ረገድ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣም ጠይቀዋል። የተለያዩ ብሔሮች በጋራ አብረው ሲኖሩ ሰላም እንደነበራቸው ያስታወሱት የመድረኩ ተሳታፊዎች ከቅርብ አመታት ወዲህ ብሔርን ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል በመጀመሩ እርስ በርስ ግጭት ውስጥ መግባት መጀመሩን ተናግረዋል። በአካባቢያቸው ግጭቶች ሲፈጠሩ የጸጥታ አካላት ሰላምን በማስከበር በኩል እንደሚዘገዩም አንስተዋል። ግጭቶችን በህዝቡ እንዲፈታ መደረጉ ጥሩ ቢሆንም የማስተባበርና የመምራት ሚናውን የሚወስድ አካል ባለመኖሩ አስታራቂ መጥፋቱን ጠቅሰዋል። ''በመሆኑም  ጸጥታን ከማስከበር ጀምሮ ችግሩን አጥንቶ መፍትሄ በማስቀመጥ በኩል መንግስት ሃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም'' ሲሉ ወቅሰዋል። መንግስት እያከናወናቸው ካሉት የለውጥ ስራዎች መካከል አንዱ 'የሰላም ሚኒስቴር' መቋቋሙ እንደሆነ በመግለጽ ርምጃውን አድንቀው ሚኒስቴሩ በጥናት ላይ በመመስረት በየአካባቢው የተፈጠሩ ቁርሾዎችን ለመፍታት እርቅ ለማውረድ መስራት እንዳለበት ጠቁመዋል። የመድረኩ ተሳታፊዎች በግጭት ምክንያት እየተከሰቱ ያሉ የመንገድ መዘጋት፣ የሸቀጦች እጥረትና ሌሎች ችግሮችንም አንስተዋል። ኢትዮጵያውያን በሃይማኖት፣ በብሄር ይለያዩ እንጂ አንድ የሚያደርጋቸው ኢትዮጵያዊነትን ለማጠናከር ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም