ቀጥታ፡

በአፍሪካ ቀንድ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የበኩላችንን እንወጣለን-- የምስራቅ አየር ኃይል አባላት

ድሬዳዋ ጥቅምት 28/2011 የኢትዮጵያ የአየር ክልል ከማንኛውም ጥቃት እንዲጠበቅና በአፍሪካ ቀንድ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የበኩላቸውን እንደሚወጡ በኢትዮጵያ አየር ኃይል የምስራቅ ምድብ አባላት ተናገሩ፡፡ በቢሾፍቱና በድሬዳዋ በሚገኘው የምስራቅ አየር ኃይል ለሁለት ዓመታት ሰልጥነው የተመረቁት የቻድ ዜጎች በበኩላቸው ኢትዮጵያ የሰጠቻቸው ሥልጠና የሁለቱን ሀገሮች ሁለንተናዊ ትስስር በማጠናከር ረገድ አስተዋጽኦው የጎላ እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡ የምስራቅ አየር ኃይል በኤስ ኤፍ መሰረታዊ የበረራ ማሰልጠኛ የተመረቁ አብራሪዎችና በሶማሊያ ተልዕኮአቸውን አጠናቀው የተመለሱ የምድቡ አባላት ለኢዜአ እንደገለፁት የአገሪቱን የአየር ክልል ከማንኛውም ጥቃት ለመጠበቅ ዝግጁ ናቸው፡፡ በኤስ ኤፍ 260 የመጀመሪያ ደረጃ በረራ የተመረቀው ካዲት ዮሃንስ ተገኝ በሰጠው አስተያየት በንድፈ ሃሳብና በተግባር ታግዞ የተሰጠው ሥልጠና ቀጣይ ተልዕኮዎቹን በብቃትና በራስ መተማመን ለመወጣት እንደሚያስችሉት ተናግሯል፡፡ ‹‹የሀገሬን አየር ክልል ከባልደረቦቼ ጋር በአስተማማኝ መንገድ ለመጠበቅ ዝግጁ ሆኛለሁ ፤ እስከ ህይወት መስዋዕትነት በመክፈል የሀገሬን ሰላምና ዕድገት አስቀጥላለሁ ›› ብሏል፡፡ በሶማሊያ ግዳጃቸውን ጨርሰው የመጡት የምድቡ አባላት አስተባባሪ ሌተናል ኮሎኔል ሃብቶም ዘነበ በበኩላቸው ''በሀገራችንና ለሶማሊያ  ወንድም ህዝብ የፀጥታና የሰላም እንቅፋት የሆነውን አልሸባብ ላይ አኩሪ ድል ማስመዝገብ ችለናል'' ብለዋል፡፡ ''በተለይ ባለፈው ነሐሴ ወር በገብረሃሬ፣ በሁርኩት፣ በሉቅ፣ በኑርፋና፣ በሂልገና ሌሎች አካባቢዎች በአልሸባብ ላይ የተገኘው አኩሪ ድል በአፍሪካ ቀንድ መረጋጋትና የጋራ ዕድገት ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት የሰመረ ያደርገዋል'' ብለዋል፡፡ እንደሌተናል ኮሎኔል ሃብቶም ገለጻ ድሉ የሽብር ጥቃት የሚሰነዝሩ አካላት እጃቸውን እንዲሰበስቡ የሚያደርግና በሀገራችን የተጀመረው የሰላም፣ የአንድነትና የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል ያግዛል ፡፡ በኢትዮጵያ አየር ኃይል የምስራቅ አየር ኃይል ምድብ ዋና አዛዥ ኮሎኔል አበበ ተካ ''ምድቡ ከሌሎች ክፍሎች ጋር በመቀናጀት የተሰጠውን ተልዕኮ በታላቅ ወኔ በመፈጸም ህዝብና መንግስትን ያኮራ ገድል በአልሸባብ ላይ ፈፅሟል'' ብለዋል፡፡ ምድቡ መሰል ተልዕኮውን ለመወጣት ዘመኑ የሚጠይቀውን የአየር ውጊያ አቅም በመገንባት የበረራ ሥልጠናዎችን ማጠናከሩን ነው ኮሎኔል አበበ ያስታወቁት፡፡ ባለፈው ቅዳሜ ከተመረቁት አራት የቻድ ዜጎች መካከል በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀው ወጣት ጆርዌ ጋሞ ዲዜሬ ሀገራችን ለሰጠቻቸው የስልጠና እድል አመስግኖ በስልጠናው ሂደት ደስተኛ እንደነበር ገልፃል፡፡ በምድር ላይ የማይቻል ምንም ነገር እንደሌለ የገለፀው ጆርዌ በስልጠናው ሂደት ሁሉም ሰልጣኞች ያጋጠሟቸውን ችግሮች ተቋቁመው  ለታላቅ ሀገራዊ ተልዕኮና ክብር ዝግጁ መሆናቸው እንደሚያረካው ተናግሯል፡፡ ''ኢትዮጵያ ለቻድ ዜጎች የሰጠችው ሥልጠና የሁለቱን ሀገሮች ሁለንተናዊ ትስስር ያጠናክረዋል፤ መሰል የሥልጠና  ትብብር ይቀጥላል ብዬ አምናለሁ'' ብሏል፡፡ ባለፈው ቅዳሜ በኤስ ኤፍ 260 አውሮፕላን በመጀመሪያ ደረጃ በረራ ሰልጥነው ከተመረቁት 12 አብራሪዎች መካከል 8ቱ ኢትዮጵያውን ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም