በደሴ ከተማ የሰባት ዓመት ሕጻን ልጅ መገደሏን ተከትሎ የተከሰተው አለመረጋጋት ወደሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተመለሰ ነው

63
ደሴ  ጥቅምት 28/2011 በደሴ ከተማ በተለምዶ "ሳላይሽ" እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሰባት ዓመት ሕጻን ልጅ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደሏን ተከትሎ ዛሬ ጠዋት በከተማዋ አለመረጋጋት ተስተውሎ ቆይቷል። በርካታ ቁጥር ያላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ድርጊቱን ፈጽሟል በሚል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለው የሟች እንጀራ አባት በመንግስት በኩል የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድበት አደባባይ ወጥተው ጠይቀዋል። በከተማዋ በተለይ ፒያሳና ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ አካባቢዎች በርካታ ሰዎች በተፈጸመው ድርጊት ዛሬ ጠዋት የተቃውሞ ድምጻቸውን ያሰሙ ሲሆን በተለይ እናቶችና ወጣቶች የሟችን ፎቶ ግራፍ በመያዝ ሀዘናቸውን ገልጸዋል። ነዋሪዎች ወደአደባባይ መውጣታቸውን ተከትሎ ለተወሰኑ ሰዓታት የትራንስፖርት እንቅስቃሴው በከተማዋ ተስተጓጉሎ ነበር። በአሁኑ ወቅት በከተማዋ አንጻራዊ መረጋጋት የተፈጠረ ሲሆን የትራንስፖርት እንቅስቃሴውም ወደነበረበት እየተመለሰ ነው። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከከተማው ፖሊስ ስለጉዳዩ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት በስልክና በአካል ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። በቀጣይ በጉዳዩ ላይ የሚመለከታቸው አካላትን በማነጋገር ተጨማሪ መረጃውን ለህዝብ እንደሚያደርስም ያስታውቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም