በአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ አጥጋቢ ሥራ እየተሰራ አለመሆኑ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
በአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ አጥጋቢ ሥራ እየተሰራ አለመሆኑ ተጠቆመ
ባህር ዳር ጥቅምት 28/2011 በአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ አጥጋቢ ሥራ እየተሰራ አለመሆኑን የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ ገለጸ። ኤጀንሲው የልማት ዘርፉን የ2011 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ላይ ከፌደራልና ክልል ባለድርሻ አካላትና ከህዝብ ክንፍ ጋር በመሆን በባህር ዳር ከተማ መክሯል። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ ለኢዜአ እንደገለጹት መንግስት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም ህብረተሰቡ በዘርፉ ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል በመረዳት በኩል ሰፊ ክፍተት አለ። ይህ በመሆኑ ዘርፉ አገሪቱ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የምታደርገውን ጥረት በሚፈለገው ልክ እያገዘ አለመሆኑን ነው የጠቆሙት። በአገሪቱ 9 ሺህ አነስተኛና 3 ሺህ መካከለኛ ማኑፋክተሪንግ ኢንዱስትሪዎች ቢኖሩም ሥራቸውን በሚፈልገው የክህሎት ደረጃ እያከናወኑ አለመሆኑን ተናግረዋል። አቶ አስፋው እንዳሉት በአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የሚሰማራውን የሰው ኃይል ያፈራሉ ተብለው የተቋቋሙ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በክህሎትና በአመለካከት ብቁ የሆነ የሰው ኃይል በማፍራት በኩል የጎላ ክፍተት አለባቸው። በአገሪቱ ያሉት ኢንዱስትሪዎች ውስን መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በትላልቅ ከተሞች ብቻ የተወሰኑ መሆናቸው በራሱ ክፍተት እየፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል። በእዚህም በዞንና በወረዳዎች የሚገኝና በቴክኒክና ሙያ የተመረቀው አብዛኛው የሰው ኃይል ክህሎትና እውቀቱን የሚያዳብርበት አጋጣሚ እያጣ መሆኑን ነው የገለጹት። " የአመለካከቱ ክፍተት ሰፊ ቢሆንም ግንዛቤው ተፈጥሮላቸው ወደ ዘርፉ የተቀላቀሉት ለውጪ ገበያ የሚቀርብ ምርት የማምረት አቅም የላቸውም፤ የውጪ ገበያን ሰብሮ ለመግባት የሚያስችል ክህሎትም አላገኙም " ብለዋል አቶ አስፋው። በመድረኩ ላይ የዳሰሳ ጥናት ያቀረቡት የኤጀንሲው ጥናትና ስልጠና ዳይሬከተር አቶ ባዝዘው አቸነፍ እንደገለጹት ጥናት ከተካሄደባቸው 222 የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ባለቤቶች ውስጥ 22 በመቶ የሚሆኑት የትምህርት ደረጃቸው 12ኛ ክፍልና ከዛ በታች ነው። "ከ95 አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች መካከል 18 በመቶዎቹ የሚሆኑት ከቴክኒክና ሙያ የተመረቁ መሆናቸውን በተካሄደው ጥናት ተረጋግጧል" ብለዋል። ዘርፉ በብቁ ባለሙያና ክህሎት ባለመመራቱ የኢንዱስትሪ ባለቤቶችም ሆኑ አገሪቱ ከዘርፉ በሚገባ እየተጠቀሙ እንዳልሆነ አስረድተዋል። አቶ ባዝዘው እንዳሉት ጥናት ከተካሄደባቸው 222 የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች መካከል ምርቶቻቸውን ወደውጪ እየላኩ ያሉት 11 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። የዘርፉ አንዱ ዓላማ የውጪ ምንዛሬን ማስገኘት ቢሆንም በክህሎት እጥረት ምክንያት ጥራቱን የጠበቀ ምርት አምርቶ ለውጭ ገበያ በማቅረብ በኩል የጎላ ችግር አንዳለ አመልክተዋል። በመሆኑም ዘርፉን ለማሳደግና አገሪቱን ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የትምህርት ተቋማት ለሰልጣኞቻቸው እውቀትን ብቻ ሳይሆን ክህሎትንና አመለካከትን ጎን ለጎን ማስረጽ ይጠበቅባቸዋል ሲሉ አቶ ባዝዘው ገልጸዋል። ከጥቅምት ከ26 ጀምሮ ለአራት ቀናት በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ባለው የውይይት መድረክ ላይ የዘርፉን ችግሮችን በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። በመድረኩም የክልልና የፌዴራል ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ነው።