የቤተክርስቲያኑዋ ሁለተኛው ዙር የሰላምና አንድነት ጉባኤ ተልእኮውን በውጤት ማጠናቀቁን ገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
የቤተክርስቲያኑዋ ሁለተኛው ዙር የሰላምና አንድነት ጉባኤ ተልእኮውን በውጤት ማጠናቀቁን ገለፀ
አዲስ አበባ ጥቅምት27/2011 በአገር ውስጥና በውጭ ያሉትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶሶች አንድ ለማድረግ ስራውን የጀመረው ሁለተኛው ዙር የሰላምና አንድነት ጉባኤ ተልእኮውን በውጤት ማጠናቀቁን አስታወቀ። ጉባኤው ከ2009 ዓ.ም የካቲት ወር ጀምሮ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶሶች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት ለመፍታት ጉባዔ መቋቋሙን ይታወቃል። ጉባዔዉ እርቀ ሰላሙን ለማምጣት በሚንቀሳቀስበት ወቅት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከተለያዩ አካላት አግኝቷል፤ ከዚሁ ከተገኝው የ117 ሺህ 454 የአሜሪካን ዶር ውስጥ 69 ሺህ ዶላሩን ለዚሁ ተግባር ማዋሉንም አመልክቷል። ቀሪውን የ48 ሺህ 419 ዶላር ደግሞ በቅርቡ በጂግጂጋ፣ በቡራዩና በአሶሳ ተፈጥሮ በነበረው ችግር ለተጎዱ ወገኖች እንዲውል መወሰኑን ነው የገለጸው። ጉባኤው ስራውን ማጠናቀቁን አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በቤልጄም የተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪና የኮሚቴው ፀሐፊ ቀሲስ ዶክተር መዝገቡ ካሳ እንዳሉት በሲኖዶሶቹ መካከል ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት ለመፍታት በርካታ አካላት ተሳትፎ አድርገዋል። ከዚህ ውስጥም ቤተክርስቲያኑዋ የነበሩባትን አለመግባባቶች ያለማንም ጣልቃ ገብነት በራሷ እንድትፈታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ያበረከቱት አሰተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ጉባኤው ምስጋናውን እንደሚያቀርብ ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጉባኤው በተለይም በአገር ውስጥ የተከፈተውን ቅርንጫፍ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴን በማነጋገር ከአንድ የአገር መሪ የሚጠበቀውን ቀና ትብብርና ድጋፍ ማድረጋቸውንም አብራርተዋል። ጉባኤው በአውሮፓና በአሜሪካ 24 በኢትዮጵያ ደግሞ 7 አባላትን አቋቁሞ ለእርቀ ሰላሙ ስኬት ሲንቀሳቀስ የቆየ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የተመሰረተበትን ዓላማ በውጤት ማጠናቀቁን አመልክተዋል። ጉባኤው በዚሁ ወቅት ለእርቀ ሰላሙ ውጤት አስተዋጽኦ ላበረከቱት አብያተ ክርስቲያናትና ከፍተኛ ድጋፍ ላደረጉ ምእመናን በእግዚአብሔር ስም መስጋናውን እንደሚያቀርብም አስረድተዋል።