ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞችን ምጣኔ ኃብታዊ ተሳትፎ ለማጠናከር እንቅስቃሴ ተጀምሯል ተባለ

አዲስ አበባ ጥቅምት 27/2011 በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ አገራት ስደተኞችን ምጣኔ ኃብታዊ ተሳትፎ ለማጠናከር እንቅስቃሴ መጀመሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለፀ። የስደተኞችን ምጣኔ ኃብታዊ ተሳትፎ ለማጠናከር የግሉ ዘርፍ ሚና ወሳኝ መሆኑን በስደተኞች ጉዳይ ላይ የተሰማሩ ተቋማት ጠቅሰዋል። የግል ባለኃብቶች፣ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የተሳተፉበትና በስደተኞች ምጣኔ ኃብታዊ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ውይይት  ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተካሂዷል። የተለያየ አገር ዜግነት ያላቸው ከ9 መቶ ሺህ በላይ የተመዘገቡ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች በኢትዮጵያ ይኖራሉ። ከእነዚህ መካከልም 44 በመቶ የሚሆኑት በጋምቤላ ክልል የሚኖሩት የደቡብ ሱዳን ሰደተኞች ናቸው። ኢትዮጵያን ጨምሮ የዓለም አገራት የሚያስጠልሏቸውን ስደተኞች የምጣኔ ኃብትና ማህበራዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ስደተኞቹን ከተረጂነት ለማላቀቅ የሚያስችል ስምምነት ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ፈርመዋል። "ሁሉን አቀፍ የስደተኞች ድጋፍ መርሃ ግብር" የሚሰኘውን የመንግስታቱ ድርጅት መርሃ ግብር ለማስፈጸም የሚያስችል የሙከራ ትግበራ በኢትዮጵያ ተጀምሯል። በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ተወካይ ሲሌሜንቲን ኒኪዌታ ስድተኞች በአገራቸው በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው የነበሩና ጉልህ ሚና ማበርከት የሚችሉ መሆናቸውን ዕውቅና መስጠት ይገባል ብለዋል። በመሆኑም ስደተኞቹን ያስጠለሉ አገራት መንግስታትና የግሉ ዘርፍ በጋራ በመሆን ስደተኞቹን በምጣኔ ኃብታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሳተፉ ቢያደርጓቸው ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አመልክተዋል። የዚህ ዓይነቱን እርምጃ የወሰዱ አገራት በርካታ ጠቀሜታዎችን ማግኘታቸውን ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩ ነው የገለጹት። ግብርና፣ የእንስሳት አርባታ፣ የማምረቻ ዘርፍና የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክቶች ስደተኞች ተሳትፈውባቸው ውጤት ካመጡባቸው የምጣኔ ኃብት መስኮች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ስደተኞች ከሰብዓዊ እርዳታ ጥገኝነት ተላቀው የትምህርትና የስራ እድል ተጠቃሚ በመሆን ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ በስደተኝነት ለሚኖሩበት አገር ብቻ ሳይሆን ወደ አገራቸው ሲመለሱም ለአገራቸው ልማት ጉልህ ሚና መጫወት ይችላሉ በማለትም አስረድተዋል። "ሁሉን አቀፍ የስደተኞች ድጋፍ መርሃ ግብር"ን ለማስፈጸም ኢትዮጵያ የመሪነት ሚና በመያዝ እየሰራች መሆኑን ነው የመንግስታቱ ድርጅት ተወካይ የገለፁት። መርሃ ግብሩ ስደተኞች ከመጠለያ ውጭ እንዲኖሩ፣ ግብርናን ጨምሮ በተለያዩ ስራዎች እንዲሰማሩ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፍጠርን ያካትታል። ከዚህም ሌላ የትምህርትና የጤና አገልግሎት  እንዲሁም የልደትና የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችልም ነው። መርሃ ግብሩን ለማስፈጸም የሚያስችል መዋቅር የተዘጋጀ ሲሆን መንግሰታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ጨምሮ የልማት አጋሮችንና ሌሎች ወሳኝ አካላትን ያከተተ ኮሚቴም ተሰይሟል። በውይይቱ የተሳተፉ የግል ባለኃብቶች  በሰጡት አስተያየት በመርሃ ግብሩ ለመሳተፍ በመጋበዛቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው ለውጤታማነቱ የበኩላቸውን ሚና ለመጫወት ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል። በጋራ መስራት የሚቻልበት አሰራር ላይ ግልጽ መመሪያ ሊኖር ይገባልም ብለዋል። በስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ስር የተቋቋመው ሁሉን አቀፍ የስደተኞች ድጋፍ መርሃ ግብር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍስሃ መብራቱ እንደተናገሩት ስደተኞችን በምጣኔ ኃብታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሳተፉ ማድረግ እንዲቻል የተቀረፀው የህግ ማዕቀፍ በቅርቡ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል። ብሄራዊ ሁሉን አቀፍ የስደተኞች ድጋፍ ስትራቴጂ  እየተዘጋጀ  መሆኑንም አክለዋል። ጽህፈት ቤቱ ለ30 ሺህ ስደተኞች የስራ እድል ለመፍጠር እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም