ቀጥታ፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአምስት አምባሳደሮች የቋሚ ተጠሪነት ሹመት ሰጠ

አዲስ አበባ ጥቅምት 27/2011 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአዲሱ መዋቅራዊ አደረጃጀት ለአምስት አምባሳደሮች የቋሚ ተጠሪነት ሹመት ሰጠ። ሚኒስቴሩ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ ቋሚ ተጠሪ ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ወይንሸት ታደሰ፣ አምባሳደር ማህሌት ኃይሉ፣ አምባሳደር ዶክተር ቦጋለ ቶሎሳ፣ አምባሳደር ነጋ ፀጋዬና አምባሳደር ደዋኖ ከድር ናቸው። አምባሳደር ወይንሸት በሲዊዲን የኢፌዲሪ ኤምባሲ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደርና እስካሁን በአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል። በተጨማሪም በኒውዮርክ የኢፌዲሪ ቋሚ መልዕክተኛ ጽህፈት ቤት ምክትል የሚስዮን መሪ በመሆንም አገልግለዋል። አምባሳደር ዶክተር ቦጋለ ቶሎሳ በኩባ የኢፌዲሪ ኤምባሲ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር እንዲሁም ወደ ዋናው መስሪያ ቤት ተመልሰውም የቆንሲላ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል ሆነው አገልግለዋል። አምባሳደር ነጋ ፀጋዬ በፈረንሳይ የኢፌዲሪ አምባሳደርና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጄነራል በመሆንም ሰርተዋል። አምባሳደር ደዋኖ ከድር በኩባ የኢፌዲሪ አምባሳደር እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን እንዳገለገሉ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል። አምባሳደር ወይንሽት ታደሰ የአፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ጉዳዮች ቋሚ ተጠሪ፤ አምባሳደር ማህሌት ኃይሉ የአውሮፓ፣ የአሜሪካ፣ የኤዥያ እና የባለብዙ ወገን ጉዳዮች ቋሚ ተጠሪ ሆነው ተሹመዋል። አምባሳደር ዶክተር ቦጋለ ቶሎሳ የዳያስፖራና ቆንሲላ ጎዳዮች ቋሚ ተጠሪ፣  አምባሳደር ነጋ ፀጋዬ የኃብት ማስተዳደርና አገልግሎት ቋሚ ተጠሪ እንዲሁም አምባሳደር ደዋኖ ከድር ደግሞ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ቋሚ ተጠሪ ሆነዋል። ቋሚ ተጠሪዎቹ በተለያዩ አገሮች እንደሚሰራው ሁሉ የመስሪያ ቤቱን የዕለት ተዕለት ስራ የመከታተልና ውሳኔ የማሳለፍ ሃላፊነት ይኖራቸዋልም ተብሏል። ስራና ሰራተኞችን ለማገናኘትና ተቋሙ ለዘመኑ የሚመጥን ቁመና እንዲኖረው የተለያዩ የለውጥ ስራዎችን እያከናወነ እንደሆነም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም