ማይጨው ሆስፒታል ለ67 ሕሙማን ነፃ የቀዶ የሕክምና ሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
ማይጨው ሆስፒታል ለ67 ሕሙማን ነፃ የቀዶ የሕክምና ሰጠ
ማይጨው ጥቅምት 27/2011 ከፍለው ለመታከም ለማይችሉ 67 ሕሙማን ነፃ የቀዶ ጥገና የሕክምና አገልግሎት መስጠቱን የማይጨው ለምለም ካርል ሆስፒታል አስታወቀ። በተደረገላቸው የህክምና እርዳታ ከህመማቸው መፈወሳቸውን ህሙማን ገልፀዋል። የሆስፒታሉ ስራአስኪያጅ አቶ ኪደ ተክሉ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ የቀዶ ህክምና አገልግሎቱ የተሰጣቸው ለማህፀን፣ ለእንቅርት፣ ለሪህና ለአጥንት ስብራት ህሙማን ነው ። ሆስፒታሉ ከቤልጂየም ሪቫይቭ ሚሽን የሕክምና ቡድን አባላት ጋር በመተባበር ህክምናው መስጠቱን ተናግረዋል ። ሆስፒታሉ በመጭው አመት ለ700 ሕሙማን ተመሳሳይ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ስምምነት ከህክምና ቡድኑ ጋር መፈራረሙን ገልፀዋል ። እንደ ስራ አስኪያጁ ገለጻ ባለፈው ዓመት ለ147 ችግረኛ ሕሙማን ነፃ የቆዶ ጥገና ሕክምና አገልግሎት ተሰጥቷል ። በሆስፒታሉ የቀዶ ጥገና ክፍል ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ ተክላይ ገብረዮውሃንስ በበኩላቸው የውጪ የሕክምና ቡድኑ አባላት ካደረጉት ሙያዊ ድጋፍ በተጨማሪ የህሙማኑን የህክምናና የመድሃኒት ወጪ መሸፈንናቸውን ተናግረዋል ። "የህክምና ቡድን አባላቱ ለሆስፒታሉ ሙያተኞች በአዳዲስ የቀዶ ህክምና መሳሪያዎች አጠቃቀም ልምድ አካፍለዋል" ብለዋል ። በቤልጂየም ሪቫይቫል ሚሽን የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ አድሃኖም ደገፋ የህክምና ቡድኑ ወደ አገሩ ሲገባ በኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን እውቀና ያገኘ መሆኑን ተናግረዋል ። ለህሙማኑ በተሰጠው ነጻ የህክምና አገልግሎት 3 ሚሊዮን ብር ወጭ መደረጉን ጠቁመዋል ። የሕክምና ቡድኑ ከአሁን በፊት በአማራ ክልል ከሚገኙ ሶስት ሆስፒታሎች ጋር በመተባበር 4 ሺህ ለሚሆኑ በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሕሙማን ተመሳሳይ የህክምና ድጋፍ ማድረጉን ተወካዩ አስታውሰዋል። የማይጨው ከተማ ነዋሪ ወጣት ተስፋአለም ጌታቸው "ለነበረብኝ የነርቭ በሽታ ህክምና ለማግኘት በሀገር ውስጥ የግል ሆስፒታሎች 60 ሺህ ብር በመጠየቄ ሳልታከም ቆይቻለሁ " ብሏል ። በቡድኑ በተደረገለት የነጻ ቀዶ ህክምና ከህመሙ ማገገሙን ተናግሯል ። በህጻንነቱ እግሩ ላይ ባጋጠመው ስብራት በአጥንት መጣመም ተቸግሮ መቆየቱን የተናገረው ደግሞ የኦፍላ ወረዳ ነዋሪ ወጣት መንገሻ ከበደ ነው። "ቤተሰቦቼ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው በመሆኑ የተሻለ ሕክምና ሳላገኝ ቆይቻለሁ፤ አሁን ባገኘሁት ነፃ ህከምና የመዳን እድል አግኝቻለሁ" ብሏል።