በጉጂ ዞን የተሻለ ምርት የሚሰጡ የሰብልና የስራ ስር ዝርያዎች በአርሶ አደሮች ማሳ እየተባዛ ነው

62
ነገሌ ጥቅምት 26/2011 በኦሮሚያ ጉጂ ዞን ከተለምዶው የተሻለ ምርት የሚሰጡ ሶስት የሰብልና አንድ የስራ ስር ዝርያዎች በአርሶ አደሮች ማሳ እየተባዛ መሆኑ ተገለጸ፡፡ የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት እንዳለው ብዛቱ እየተካሄደ ያለው የአካባቢው  አርሶ አደሮችም የሚገጥማቸውን የዘር እጥረት ለማቃለል ነው፡፡ እነዚህ የገብስ፣ የስንዴ ፣የባቄላና ድንች ዝርያዎች  ከቦሬ ግብርና ምርምር ማዕከልና  ስንዴ ደግሞ ከአሰላ ምርጥ ዘር ድርጅት የተገኙ ናቸው ብለዋል። በአርሶ አደሩ ማሳ ከሚገኙት ዝርያዎች መካከል ገብስ  35፣ ስንዴ 40 ባቄላ ደግሞ እስከ  25 ኩንታል  ምርት በሄክታር እንደሚሰጡ በጽህፈት ቤቱ  የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ አወል ቃሲም ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡ የሰብል ዝርያዎቹ ከተለምዶው  በእጥፍ ያህል ብልጫ እንዳላቸውና የድንች ምርጥ ዘር ደግሞ በሄክታር እስከ 200 ኩንታል ምርት በመስጠት የተሻለ መሆኑን አመላክተዋል። የሰብልና የድንች ዝርያዎቹ  በሽታንና የተፈጥሮ ችግርን በመቋቋም ፈጥነው የሚደርሱ እንደሆኑ በሰርቶ ማሳያ የተረጋገጡ ናቸው፡፡ እንደባለሙያው ገለጻ እነዚህ ዘርያዎች ከሐምሌ 2010 ዓ.ም ጀምሮ በዞኑ  ገምሮ ፣ሀሮ ሁላቡ ፣አና ሶራና ኦዶላ ሬዴ ወረዳዎች በ29 ሄክታር የአርሶ አደሮች  ማሳ ላይ እየተባዙ ነው፡፡ ከዚህም  እስከ 850 ኩንታል ምርት ይጠበቃል፤ ይህም  የአርሶ አደሩን የምርጥ ዘር እጥረት ያቃልላል ተብሏል። በዞኑ አና ሶራ ወረዳ የሶሎሎ ቆቦ ቀበሌ አርሶ አደር  መኩሪያ ሜንቆ በሰጡት አስተያየት ከአስራ አንድ አርሶ አደሮች ጋር በመተባበር ኦጎልቾ የተባለ የስንዴ ምርጥ ዘር እያባዙ መሆኑን ተናግረዋል። ካሁን በፊት የሚጠቀሙበት የአካባቢ ዘር በዋግ በሽታ የሚጠቃ ከመሆኑን ሌላ የሚሰጠው ምርት በሄክታር ከ20 ኩንታል ያነሰ በመሆኑ በአዲሱ ምርጥ ዘር የተሻለ ምርት ይጠብቃሉ። በአዝመራ ወቅት የሚገጥማቸው የዘር እጥረትና በበሽታ መጠቃት አዲሱን ምርጥ ዘር ለማባዛት እንዳነሳሳቸውም አርሶ አደሩ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም