ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ ጫት የሚያደርሳቸውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለማቃለል የቀረበለትን ሰነድ አፀደቀ

ባህርዳር ጥቅምት 26/2011 የአማራ ክልል ምክር ቤት ጫት በክልሉ እያደረሳቸው ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለማቃለል የቀረበለትን ሰነድ አፅድቋል። የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ልዑል ዮሐንስ ሰሞኑን ለምክር ቤቱ  በክልሉ እየተስፋፋ በመጣው ጫት ያቀረቡበት ሰነድ ተክሉ የክልሉን ሕዝብ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየዳረገው መሆኑን ገልጸዋል። በእርሻ ማሳዎች በፍጥነት እየተስፋፋ የመጣው ተክል በተለይ ወጣቱ በራሱ እንዳይተማመን፣በሱስ ተጠምዶ ሥራውን በአግባቡ እንዳይሰራ፣ ራሱን እንዲጥል፣ ለስንፈተ ወሲብ እንዲጋለጥ አድርጎታል ብለዋል። ምክር ቤቱም ምርቱ በመዝናኛ ቦታዎች፣ በሆቴሎች፣ መንግሥታዊ በሆኑና ባልሆኑ ተቋማት፣ በትምህርት ቤቶችና ሌሎች ተቋማት እንዳይሸጥ፣ እንዳይቃምና እንዳይተዋወቅ ማድረግ እንደሚገባውም አሳስበዋል። መንግሥትና ኅብረተሰቡና በተክሉ ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች የሚያገኙትን ገቢ ለመተካት በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲሰማሩ እገዛ እንዲያደርጉ ምክትል ኃላፊው ጠይቀዋል። እንዲሁም ምርቱን በመሸጥና በማከፋፈል ሥራዎች የተሰማሩ አካላት በሌሎች ተግባራት ተሰማርተው ሕይወታቸውን እንዲቀይሩ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል። በጫት ሱስ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች የተዳረጉ ወገኖች ወደቀድሞ ኑሮ ሁኔታቸው እንዲመለሱ የማገገሚያ ማዕከላት እንዲቋቋሙ  አስገንዝበዋል። የምክር ቤቱ የሰው ሃብትና ቱሪዝም ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ እንደገለጹት በክልሉ ቆላማና ወይና ደጋ አካባቢዎች የሚመረተው ተክል በማህበራዊና ኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ በሚያደርሰው ጉዳት ምርቱ እንዲቆም የሕዝቡ ግፊት እየጨመረ መጥቷል። ምክር ቤቱ በተለይም አምራች የሆነውን ኃይል በማጥቃት ለችግሮች እየዳረገው በመጣው ተክል ጉዳይ ተወያይቶ ምርት፣ ዝውውር፣ ሽያጭና አጠቃቀምን የሚከለክል የህግ ማዕቀፍ እንዲያወጣ ጠይቀዋል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው ሰነዱ ለምክር ቤቱ የቀረበው አባላቱ ጫት ጎጂ መሆኑን አውቀውና የጋራ አቋም ይዘው በየደረጃው ሕዝቡን እንዲያወያዩበት መሆኑን አስታውቀዋል። ኅብረተሰቡ በጫት ላይ ክልከላ እንዲደረግ በየመድረኩ እንደሚገልጽ ያወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከል ሌሎች አማራጮችን መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል። በተለይ በጫት ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች ማሳቸውን ወደ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲያዞሩ መርዳት ያስፈልጋል ሲሉም አሳስበዋል። የምክር ቤቱ አባላት ሰነዱን በአብላጫ ድምፅ አፅድቀውታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም