ቀጥታ፡

ከ10 ዓመት በላይ ያስቆጠሩና የተበላሹ የስፖርት ትጥቆች በፌዴሬሽኑ መጋዘን ውስጥ ተገኙ

አዲስ አበባ ጥቅምት 26/2011 ከ10 ዓመት በላይ ያስቆጠሩና የተባላሹ የስፖርት ትጥቆች በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መጋዘን ውስጥ መኖራቸውን የኦዲት ሪፖርት አመላከተ። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 22ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዷል። በጉባኤው ከቀረቡት ጉዳዮች አንዱ የ2009 ዓ.ም የኦዲት ሪፖርት ሲሆን በሪፖርቱም በፌዴሬሽኑ መጋዘን ውስጥ በሚሊዮን ብር የሚቆጠር ዋጋ ያላቸው የስፖርት ትጥቆች እንዳሉ ነው ያመላከተው። ከዚህ ውጭ በኦዲት ሪፖርቱ ከሶስት የአትሌት ማናጀር ተወካዮች መሰብሰብ የነበረበት ወደ 800 ሺህ ብር የሚጠጋ ገንዝብም አልተሰበሰበም ተብሏል። የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ችግሩ መኖሩን ገልጸው አንዳንድ ጫማዎች መቆራረጥ የጀመሩም እንዳሉ ተናገሯል። የፌደሬሽኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ የስፖርት ትጥቆቹ ለክልል የስልጠና ማዕከላት ለምን በወቅቱ መስጠት እንዳልተቻለ ከኢዜአ ለቀረበላቸው ጥያቄ "የፌዴሬሽኑ ስፖንሰር የሆነው አዲዳስ ካምፓኒ አዲስ ትጥቆችን ሲያመጣ ያንን ስለሚጠቀሙ ነው" ብለዋል። ''የስፖርት ትጥቅ ስላለ ብቻም ለሚፈለጉት አካላት ብንሰጥ ተጠያቂነት ስለሚያስከትል ነውም'' ብለዋል። ብዙ ዓመት ያስቆጠሩ የስፖርት ትጥቆችን ኮሚቴ ተቋቁሞ የዋጋ ተመን ከወጣ በኋላ በፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ አልያም በጠቅላላ ጉባኤው ተወስኖ ለአትሌቲክስ ስልጠና ማዕከላት ለልምምድ ጊዜ እንዲለብሱት ይሰጣቸዋል ተብሏል። ለአንጋፋ አትሌቶች የሚሆኑ ካሉም ለእነሱ የሚሰጡ ሲሆን አገልግሎት ላይ መዋል የማይችሉት ደግሞ የሚወገዱ ይሆናል ብለዋል። ይህን ለማድረግ ግን ቅድሚያ ቆጠራ የሚያካሄድና የዋጋ ተመን የሚያወጣ ኮሚቴ ማቋቋም ያስፈልጋል ያንንም ኮሚቴ የማቋቋም ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል። ከዚህ ውጭ በኦዲት ሪፖርቱ ከቀረቡት ሁለተኛው ጉዳይ ፌዴሬሽኑ ከማናጀሮች ለምን ገንዝብ እንዳልሰበሰበ ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ  በሰጠው ምላሽ ማናጀሮቹን እንዲከፍሉ መጠየቃቸውንና ነገር ግን ብዙም  ገፍተው እንዳልሄዱበት ነው የገለጸው። ማናጀሮቹን መጠየቁን ገፍተን በመሄድ  800 ሺህ ብር እንዲከፍሉ ያልተጫናቸው ከዚህ ገንዘብ በላይ በሚሊዮን የሚቆጠር የገንዝብ ጥቅም እያስገኙልን በመሆናቸውም ነው ብሏል። በተለይም ለአትሌቶች የውድድር እድል በመፍጠርና ሌሎች አንዳንድ የፌዴሬሽኑ ስራዎች ላይ ጥሩ ነገር እያበረከቱ በመሆኑም ነው ብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም