ቀጥታ፡

የውሹ የአሰልጣኝነት የደረጃ ማሻሻያ ፈተና ተጀምሯል

አዲስ አበባ ጥቅምት 26/2011 የውሹ የአሰልጣኝነት ደረጃን ለማሻሻል የሚያስችል የፈተና መርሃ ግብር ዛሬ በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ተጀመረ። በፈተናው በሁለቱም ጾታዎች ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ 209 አሰልጣኞች እየተሳተፉ ነው። ከፈተናው በፊት ስልጠና የሚሰጥ ሲሆን ፈተናውን በብቃት የሚወጡ አሰልጣኞችም ባሉበት አካዳሚ የውሹ ስፖርት ማዕከላትን በመክፈት ስፖርተኞችን የማሰልጠን ፈቃድ እንደሚያገኙ ይደረጋል። ፈተናውን የሚሰጡት አሰልጣኞች የአምስተኛ ዳን ደረጃ ያላቸው ማስተር አህመድ አብዱልቃድር፣ ማስተር ተሾመ አባተ፣ ማስተር ቶፊቅ ሹሜና ማስተር ከበደ ገብሬ ናቸው። የኢትዮጵያ ውሹ ፌዴሬሽን የውድድርና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ገበየሁ ሙሉጌታ ለኢዜአ እንደገለጹት ስልጠናውና ፈተናው የሚሰጠው ደረጃቸውን ከአንድ እስከ ሶስተኛ ዳን ማሻሻል ለሚፈልጉ አሰልጣኞች ነው። ባለሙያው አክለውም በስልጠናውና በፈተናው ላይ ሁሉም ክልሎች እንዲሳተፉ ጥሪ መቅረቡንና ከጋምቤላና አፋር ክልሎች በስተቀርም ከሁሉም  ክልሎች ተሳታፊዎች መላካቸውን ተናግረዋል። ስልጠናውን ተከትሎ በሚሰጠው ፈተናም ደረጃቸውን የሚያሻሽሉት አሰልጣኞች ባሉበት አካዳሚ የውሹ ስፖርት ማዕከላትን በመክፈት ስፖርተኞችን የማሰልጠን ፈቃድ እንደሚያገኙና ይህም ብቁና ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እንደሚያግዝ አክለዋል። በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ የሚሰጠው ስልጠና እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2011 ዓ.ም ይቆያል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የውሹ ስፖርት ትልቁ የአሰልጣኝነት ደረጃ ዘጠነኛ ዳን የሚባለው እንደሆነ የዓለም አቀፉ የውሹ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም