ስሑል ሽሬ ከወላይታ ዲቻ ጋር ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ያለምንም ግብ ተለያየ - ኢዜአ አማርኛ
ስሑል ሽሬ ከወላይታ ዲቻ ጋር ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ያለምንም ግብ ተለያየ
ሸሬ እንዳስላሴ/መቀሌ ጥቅምት 25/2011 ዘንድሮ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ ያደገው ስሑል ሽሬ ከወላይታ ዲቻ ጋር በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ባደረገው የመጀመርያ ጨዋታ ያለምንም ግብ ተለያየ። በመቀሌ ከተማ ዛሬ በተካሄደው የኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታም ቡና ደደቢትን ሁለት ለባዶ አሸንፏል። ከ20 ሺህ በላይ የከተማዋ የስፖርት አፍቃሪ በተከታተለው በዚህ ጨዋታ ስሑል ሽሬ ከአቻው ወላይታ ዲቻ በሜዳው ነጥብ ጥሏል። በፕሪሜየር ሊግ ጨዋታ ልምድ ያለው ወላይታ ዲቻ በስሑል ሽረ ተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ቢደረግበትም የሚቀመስ አልሆነም። የወላይታ ዲቻ አስልጣኝ ዘነበ ፍስሃ በሰጡት አስተያየት "በአጠቃላይ ሲታይ ጨዋታው ጥሩ ነበር። ቡድናችን የተጠበቀውን እንቅስቃሴ አለማድረጉ ብቻ ሳይሆን የኳስ ፍስቱ የተበላሸ ነበር፤ ያም ሆነ ይህ ውጤቱ በአቻ መጠናቀቁ አይከፋም" ብለዋል። ቡድናቸው ጥሩ አቀባበል እንደተደረገለት የተናገሩት አስልጣኙ የስሑል ሽሬ ደጋፊዎች በጥሩ የስፖርት ስነ ምግባር ቡድናቸውን ሲደግፉ ማየታቸውን ተናግረዋል። የስሑል ሽሬ እግር ኳስ ክለብ በኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ ጨዋታው የመጀመሪያው ቢሆንም ጥሩ እንቅስቃሴ ማሳየቱንና በዚህ ከቀጠለ ወደፊት የተሻለ ተፎካካሪ እንደሚሆን ገልፀዋል። የስሑል ሽሬ አስልጣኝ ዳኒኤል ፀሐየ በበኩላቸው "ብዙ የጎል እድሎች ቢፈጠሩም ልንጠቀምባቸው ባለመቻላችን እድለኞች አልነበርንም" ብለዋል። " ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተን የእለቱ ዳኛ ከልክለውናል" ሲሉም ቅሬታቸውን ገልጸዋል። "የመጀመርያ የፕርሜየር ሊግ ጨዋታችን በመሆኑ በውጤቱ አልተከፋሁም ሲሉም አክለው" ገልጸዋል። በሌላ ዜና በመቀሌ ከተማ ዛሬ በተካሄደው የኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታ ቡና ደደቢትን ሁለት ለባዶ አሸንፏል። በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የጣለው ዝናብ የጨዋታውን እንቅስቃሴ ቢያደበዝዘውም በሁለተኛው አጋማሽ ቡና ተሽሎ በመንቀሳቀሱ ሁለት ለባዶ ማሸነፍ ችሏል። ባለሜዳው ደደቢት ካገኛቸው የግብ ዕድሎች አንዱ አግዳሚ ሲመልስበት ሌሎቹን በአግባቡ አለመጠቀሙ ተሸናፊ እንዲሆን አድርጎታል። የተሻለ እንቅስቃሴና ሙከራ ያደረገው ቡና ከእረፍት በኋላ ባስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች ጨዋታውን አሸንፎ ለመውጣት ችሏል። የደደቢት አሰልጣኝ ኤሊያስ ኢብራሂም ከጨዋታው በኋላ በሰጡት አስተያየት በጉዳት ምክንያት የጎደሉ ተጫዋቾች ቢኖሩም ባሉት ጥሩ ለመንቀሳቀስ ቢሞክሩም እንዳልተሳካላቸው ገልጸዋል። "የተጎዱት ተጨዋቾች በቀጣይ ጨዋታ ስለሚሳተፉ ጥሩ ውጤት እናስመዘግባለን" ብለዋል። "የቡና አሰልጣኝ ዲድዬ ጎሜዝ በበኩላቸው በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ አልተጫወትንም በሁለተኛው ጥሩ በመንቀሳቀሳችን ማሸነፋችን ይገባናል" ብለዋል።