የምክር ቤቱ አባላት ሰላምን በማረጋገጥና የህዝብ ለህዝብ ትስስር በማጠናከር ሚናችንን እንወጣለን አሉ - ኢዜአ አማርኛ
የምክር ቤቱ አባላት ሰላምን በማረጋገጥና የህዝብ ለህዝብ ትስስር በማጠናከር ሚናችንን እንወጣለን አሉ
ሃዋሳ ጥቅምት 25/2011 ሰላምን በማረጋገጥና የህዝብ ለህዝብ ትስስር በማጠናከር ሚናቸውን እንደሚወጡ የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳዳር አቶ ሚሊዮን ማቲዮስ በበኩላቸው ለክልሉ ሰላምና ፀጥታ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ ምክር ቤቱ ለአራት ቀናት ሲካሄድ ቆይቶ ትናንት ባጠናቀቀው ጉባዔ ከተወያያባቸው ጉዳዮች ቀዳሚው የክልሉ ጸጥታ ጉዳይ ነበር፡፡ አባላቱም የክልሉን ሰላምና ጸጥታን በማረጋገጥና የህዝብ ለህዝብን ትስስር በማጠናከር የሚጠበቅባቸውን ድርሻ ለመጫወት መዘጋጀታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስታውቀዋል፡፡ ከአቶ ካሳሁን ሙላቱ የምክር ቤት አባላት የክልሉ ህዝቦች ተወካዮች በመሆናቸው ከመንግስት፣ ከህዝብና ከፀጥታው ኃይል ጎን በመቆም ሰላም ለማስጠበቅ የተጣለብንን ኃላፊነት መወጣት አለብን ብለዋል፡፡ ሰላምን መስበክና የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ማጠናከር፣ ሃሳቦች በነፃነት እንዲንሸራሸሩ በማድረግ የሠላም አምባሳደር በመሆን ጭምር በግንባር ቀደምትነት እንደሚንቀሳቀሱ ተናግረዋል፡፡ የምክር ቤት አባላት በተለያዩ ምክንያቶች የደፈረሰውን የክልሉን ሰላም በመመለስ ረገድ ኃላፊነት አለባቸው ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ የምክር ቤት አባል የሆኑት ወይዘሮ ሜሮን ታደሰ ናቸው፡፡ በህዝብ የሚነሱ አጀንዳዎች ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ምላሽ እንዲያገኙ ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ሰላም በሚያወኩና በህገ ወጥ ተግባር ውስጥ የሚሳተፉ ወጣቶችን በመምከር ከመንግስት አመራሮች ጋር መስራት አለብን ብለዋል፡፡ ሼኸ አብዱረሂም ሲራጅ በበኩላቸው የልማት ጥያቄዎች መልስ የሚያገኙት ሰላም ሲኖር መሆኑን በመገንዘብ የምክር ቤቱ አባላት ለሰላም ዘብ መቆም ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ አባላቱ ወጣቶችን ማስተማር ዋነኛው ተግባራቸው መሆን እንደሚገባውና የኃይል እርምጃ ለመውሰድ የሚደረግ እንቅስቃሴን ቀድሞ ለመግታት መስራት ይገባል ብለዋል፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቲዮስ የለውጥ እንቅስቃሴውን ለማጠናከር የክልሉን ፀጥታ የሚያውኩ ጉዳዮችን ለማስወገድ በተለየ ትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡ በተለያዩ አከባቢዎች ከሚቀርቡ የመብት ጥያቄዎች ጎን የመንግስት ተቋማት ተግባራት በሚያውክ መልኩ መከናወኑ ተገቢነት እንደሌለው ያስገነዘቡት ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ረገድ የፀጥታው ሴክተር ስርዓት ለማስጠበቅ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ በክልሉ ያሉትን የካበቱ የሽምግልና ባህላዊ እሴቶችንና የሃይማኖት አባቶችን በመጠቀም የክልሉን አንድነትና ትስስር ማጠናከር እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡ የምክር ቤት አባላትም ከመንግስት ጎን በመሆን ሚናቸውን እንዲወጡ ርዕሰ መስተዳድሩ ጠይቀዋል፡፡