ቀጥታ፡

የውሹ የአሰልጣኝነት የደረጃ ማሻሻያ ስልጠናና ፈተና ነገ ይጀመራል

አዲስ አበባ ጥቅምት 25/2011 የውሹ የአሰልጣኝነት የደረጃ ማሻሻያ ስልጠና ነገ በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ይጀመራል። በስልጠናውና ፈተናው በሁለቱም ጾታዎች ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ከ100 እስከ 150 አሰልጣኞች ይሳተፉበታል ተብሎም ይጠበቃል። ማስተር አህመድ አብዱልቃድር፣ ማስተር ተሾመ አባተ፣ ማስተር ቶፊቅ ሹሜና ማስተር ከበደ ገብሬ ስልጠናውን የሚሰጡት አሰልጣኞች ሲሆኑ አሰልጣኞቹ የአምስተኛ ዳን ደረጃ ያላቸው ናቸው። የኢትዮጵያ ውሹ ፌዴሬሽን የውድድርና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ገበየሁ ሙሉጌታ የአሰልጣኝነት ፈተናው ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ዳን እንደሆነ ለኢዜአ ገልጸዋል። በሚሰጠው ፈተናም ደረጃቸውን የሚያሻሽሉት አሰልጣኞች ባሉበት አካዳሚ የውሹ ስፖርት ማዕከላትን በመክፈት ስፖርተኞችን የማሰልጠን ፈቃድ እንደሚያገኙና ይህም ብቁና ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እንደሚያግዝም ተናግረዋል። ስልጠናው በኢትዮጵያ ያለውን የውሹ የአሰለጣጠን ደረጃ ለማሻሻልና ሌሎች አገራት በስፖርቱ የደረሰቡትን ደረጃ አውቆ ልምድ ለመቅሰም ያግዛል ብለዋል። በተያዘው የበጀት ዓመት የዳኝነትና የአሰልጣኝነት ስልጠናዎችን ለመስጠት እቅድ መያዙም ተጠቁመዋል። በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ የሚሰጠው ስልጠና እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2011 ዓ.ም ይቆያል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የውሹ ስፖርት ትልቁ የአሰልጣኝነት ደረጃ ዘጠነኛ ዳን የሚባለው እንደሆነ የዓለም አቀፉ የውሹ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል። ውሹ የሚለው ቃል የመጣው ከቻይና  ሲሆን “ው” ማለት ወታደራዊ “ሹ” ደግሞ አርት ማለት ነው። ውሹ ከሌሎቹ የማርሻል ስፖርቶች የሚለየው እጅና እግርን እኩል በማስተባበርና የተለያዩ መሣሪያዎችን በመጠቀም የሚካሄድ የስፖርት ዓይነት በመሆኑ እንደሆነ ይነገርለታል። የውሹ ስፖርት ወደ ኢትዮጵያ በዚህ ጊዜ ወይንም በሌላ አገር ሰው ወደ አገሪቷ መጥቶ ተጀመረ ብሎ ለመናገር የሚያስችል የተደራጀ ሰነድ ባይኖርም በስፖርቱ እውቀትና ችሎታው ያላቸው ግለሰቦች በተለያዩ መጠሪያ የውሹ ስፖርትን በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1960ዎቹ ያዘወትሩትና ይለማመዱት እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም