ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ያገለገሉ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን አመስግኖ መሸኘት የመበላላት ፖለቲካን የቀየረ ነው- ተዋቂ ግለሰቦች

አዲስ አበባ  ጥቅምት 25/2011 ኢትዮጵያን በታማኝነትና በቅንነት ያገለገሉ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን አመስግኖና አክብሮ መሸኘት በአገሪቷ የነበረውን የመጠፋፋት ፖለቲካን የቀየረ መሆኑን ታዋቂ ግለሰቦች ገለጹ። ለቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ትናንት ማምሻውን በብሔራዊ ቤተ-መንግስት በተዘጋጀ የሽኝት ፕሮግራም ላይ የታደሙ ታዋቂ ሰዎች ለኢዜአ እንዳሉት  በተለያዩ የስልጣን እርከኖች ላይ ያገለገሉ ግለሰቦችን አክብሮ የመሸኘት ባህል መጀመሩ ለአፍሪካ ተምሳሌት ያደርገናል። በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በነበረው ልምድ በተለያዩ የስልጣን እርከን ላይ ያገለገሉ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እጣ ፈንታ በውጭ አገራት ተሰዶ መኖር አልያም በሀገር ውስጥ በእስር ቤት መንገላታት እንጂ ምስጋና ሲቸራቸው አይታይም። ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ  የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመና  የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን አመስግኖ መሸኘት እየተለመደ መጭጥቷል። ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ታዋቂ ግለሰቦቹ ታዲያ በኢትዮጵያ ያገለገለን የሚያከብር ባህል የዳበረ ባለመሆኑ አመስግኖ የመሸኘትን ባህል አንዲጎለብትና ለትውልድ እንደ አንድ ቅርስ ለማውረስ አሁን የተጀመሩ ሥራዎች መልካም ናቸው ብለዋል። የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በሰጡት አስተያየት"ካገለገሉ በኋላ ችግር ነበር ድሮ ሰዎች ወደ ውጪ ነው የሚሸሹት።ይሄ ቀርቷል አሁን።ያንን ማጠናከር ነው ሶስታችንም  ፕሬዚዳንቶች ነበርን   እዚሁ አገር ነው ያለነው አልተመቸንም ጥሩ አይደለም ሁኔታው ብለን ወደ ውጪ አልሄድንም። ይሄ ነው የዶክተር አብይ አካሄድ" "ይሄ ለኢትዮጵያ አዲስ ነው፤በዘመናዊ ታሪካችን ላይ ብቻ ሳይሆን በጥንታዊ ታሪካችን ላይ አንዱ የሚጎድለን መሪዎች በሰላም መቀየር  እና ነባር መሪዎች  በሰላም ሲኖሩ የማየት እድል አልነበረም ። እኔ የምመኘው  ይሄን ታሪክ ልጆች ቢያዩት ከእኛ ከአዋቂዎቹ ይልቅ ይሄ ፕሮግራም ህፃናት ባሉበት የአፀደ ህፃናትና አንደኛ ደረጃ ልጆች ባሉበት ቢከናወን እንዴት ጥሩ ነበር። ምክንያቱም እነሱ ናቸው ይሄንን ማየት ያለባቸው እንደ አዲስ መልመድ ያለባቸው ብዬ  የማምነው  "  በማለት የገለጸው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ነው በኢትዮጵያ ያገለገሉ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን አመስግኖ መሸኘት አዳዲስ በኃላፊነት የመጡ ተሿሚዎች መልካምና ዓርዓያነት ያለው እንዲሁም ለክብር የሚያበቃ ስራ እንዲሰሩ መነሳሳትን የሚፈጥርላቸው መሆኑንም ጭምር ነው የገለፁት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም