በፓርኩ ከተገነቡ ሼዶች ብዙዎቹ በባለሀብቶች ተይዘዋል

35
መቀሌ ጥቅምት 25/2011 በመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከተገነቡ የማምረቻ ሼዶች ውስጥ አብዛኞቹ በባለሀብቶች መያዛቸው ተገለፀ። በፓርኩ ከተገነቡ 15 ሼዶች መካከል 12ቱ በአምስት የውጭና በአንድ አገር ውስጥ ባለሃብቶች መያዛቸውን የፓርክ የአንድ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ ጎይቶም ገብረኪዳን ለኢዜአ ገልጸዋል። አብዛኞቹ ሼዶች ወደ ማምረት ሥራ እየተሸጋገሩ መሆናቸውን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል ። በፓርኩ ከገቡ የውጭ ባለሀብቶች ውስጥ የህንድና የስሪላንካ ኩባንኛዎች ትልቁን ስፍራ መያዛቸውን ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል። " አናንታ ግሩፕ " የተባለ የህንድ ኩባንያ ቀደም ብሎ ከያዛቸው ስድስት ሼዶች በተጨማሪ አንድ ሼድ ለመጨመር ጥያቄ ማቅረቡንም አለብነት ጠቅሰዋል። "ኤስ. ሲ. ኤም ኬንት ጋርመንት" የተባለ ሌላ የህንድ ኩባንያም በ549 ነጥብ 9 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የተከለው የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካም ወደ ማምረት ሥራ መሸጋገሩን ነው የገለጹት፡፡ አቶ ጎይቶም እንዳሉት ኩባንያው ሰሞኑን 300 ሺህ የሚሆኑ የተለያዩ አልባሳትን ወደ ፈረንሳይና ጀርመን ገበያ የላከ ሲሆን እስካሁንም ከ500 ለሚበልጡ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ " በስሪላንካውያንና በህንድ ባለሀብቶች በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የተገነቡ ሁለት የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካዎች በቅርቡ ወደ ማምረት ይሸጋገራሉ " ብለዋል ። እንደሥራ አስኪያጁ ገለጻ ኢንዱስቱሪ ፓርኩ ሙሉ በሙሉ ወደ ማምረት ሥራ ሲገባ በሁለት ፈረቃ ለ20ሺህ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራል ። በፓርኩ የሥራ እድል ከተፈጠረላቸው መካከል ወጣት ልዋም ወልዱ በሰጠችው አስተያየት በኤስ. ሲ. ኤም. ኬንት ጋርመንት ኩባንያ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በ3 ሺህ ብር ደመወዝ መቀጠሯን ገልጻለች ። "የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በመቀሌ ከተማ በመከፈቱ ወጣቶች ተጠቃሚ ሆነናል " ያለው ደግሞ ወጣት መሀሪ ሙሉብርሃን ነው። የመቀሌ ኢንዱስቱሪ ፓርክ በ92 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ግንባታው ተጠናቆ ከአንድ ዓመት በፊት በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ መመረቁ ይታወቀል፡፡              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም